የፈረንሣዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አገራቸው እስላማዊ ሸማቂዎችን በመዋጋት ላይ ከሚገኙባት ማሊ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ፣ ሆኖም በአጎራባች ምዕራብ አፍሪቃ አገሮች ሰራዊት እንደሚራት ተናገሩ። ማክሮን ፓሪስ ላይ በሰጡት በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫቸው “ዕቅድና ግባቸውን ከማንጋራቸው የማሊ የሽግግር ባለሥልጣናት ጋር ካሁን ቀደም ስናደርግ በነበረው “የወታደራዊ ትብብር ተሳትፎ መቀጠል አንችልም” ነው ያሉት።
ፈረንሣይ ማሊ ውስጥ ያሏትን 2,400 ወታደሮች ጨምሮ በሳህል ክልል በአጠቃላይ 4,300 ወታደሮች አሏት። ባርካኔ እየተባለ የሚጠራውም ፈረንሣይ-መር ኃይል በቻድ፣ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እና ሞሪታኒያ ውስጥ ተሳትፏል።
የፈረንሣይ ኃይሎች እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2013 አንስቶ በማሊ እስላማዊ ጽንፈኞችን ከሥልጣን ለማባረር የተሳተፉበትን ጨምሮ ለረዥም ጊዜ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ የቆዩ ናቸው።
በሌላ ተያያዥ ዜና የአውሮፓ መሪዎችም ማሊ ውስጥ ያለውን አውሮፓ-መር ወታደራዊ ግብረ ኃይል በተመሳሳይ የሚያወጡ መሆናቸውን ዛሬ ይፋ አድርገዋል።