የስፔይን ደህንነት ኃይሎች ከማድሪድ ውጭ በሚገኝ የአየር ኃይልጦር ሰፈር ወዳለው የአውሮፓ ህብረት የሳተላይት ማዕከል በደብዳቤ ውስጥ ተደብቆ ለአራተኛ ጊዜ መላኩ የተጠረጠረ ፈንጂ ማግኘታቸው ተነገረ።
ደብዳቤው በአየር ኃይሉ የደህንነት ኃይሎች ሲመረመር በውስጡ ተቀጣጣይ ነገሮችን መያዙ ተመልክቷል።
የስፔይን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ ጽ/ቤት እአአ ጥቅምት/24 እንዲሁም ስፔይን የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ እና የስፔይን ጦር መሳሪያ አምራች ድርጅት ትናንት ረቡዕ ካገኟቸው ደብዳቤዎች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የሳተላይ ማዕከሉ በህዋ ከሚገኙ የስለላ ሳተላይቶች መረጃዎችን በመቀበል ለአውሮፓ ህብረት የጋራ የውጭና የደህንነት ፖሊሲዎችን ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑን በዘገባው ተገልጿል።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦረል ባለፈው መስከረም ማዕከሉን የአውሮፓ ዐይን ሲሉ መጥራታቸው ተነግሯል።
በደብዳቤው ውስጥ የተላከው ቦምብ ትናንት ረቡዕ በስፔይን ማድሪድ ለሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ እና ዛራጎዛ ውስጥ ለሚገኘው ኢንስታላዛ ለተባለው ለስፔይን የጦር መሳሪያ አምራች ድርጅትም የደረሰ መሆኑን ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኢንስታላዛ ሲ90 የተባሉ ሮኬት አስወንጫፊ መሳሪያዎችን የሚያመርት ድርጅት ሲሆን ስፔይን መሳሪያዎቹን ለዩክሬን መለገሷ በዘገባው ተጠቅሷል።
እስካሁን ከተላኩት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የመቁሰል አደጋ ያስከተለው የደብዳቤው ውስጥ ቦምብ ትናንት በዩክሬን ኤምባሲ ሠራተኛ ላይ የደረሰው መሆኑም ተነግሯል።
የስፔይን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድርጊቱ ሽብርተኝነት ሊሆን ይችላል በሚል ጉዳዩን የሚያይበት ፋይል መክፍቱ ተመልክቷል።