አዲስ አበባ - ዋሺንግተን ዲሲ —
በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ትናንትና ዛሬ በተፈጠሩ ግጭቶች ብዙ ሕይወት መጥፋቱን የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት - መኢአድና ከየአካባቢው ያነጋገርናቸው ሰዎች ገልፀዋል፡፡
ባለፉት ሰባት ቀናት ውስጥ በአማራ ክልል 28፣ በኦሮምያ 17 ሰው መገደሉን መኢአድ አስታውቋል፡፡
ዛሬ ከተገደሉት አማራ ክልል ውስጥ አራቱ የፀጥታ ኃይል አባላት መገደላቸው ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ዳንግላ ላይ የከተማዪቱን ከንቲባና የወረዳ አስተዳዳሪውን መኖሪያ ቤቶች ጨምሮ አምስት ቤቶች መቃጠላቸው ተገልጿል፡፡
ዛሬ፤ ሰኞ ብዙ ሕይወት እንደጠፋባት በተነገረው በስማዳ የፀጥታ ኃላፊውን ለማነጋገር የተደረገው ሙከራ አልተሣካም፡፡
የክልሉ መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለቪኦኤ በሰጡት ቃል በክልሉ ውስጥ በሕይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱንና የተደራጁ እንቅስቃሴዎችም መኖራቸውን ገልፀው መንግሥት ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ስለሁኔታው ዝርዝርና የተዘጋጀ መረጃ የክልሉ መንግሥት በቅርቡ እንደሚሰጥ ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
ለዝርዝርና በርከት ያሉ ተጨማሪ መረጃዎች የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡