በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዶናልድ ትራምፕ በቀድሞ ጠበቃቸው ማይክል ኮኸን ሊመሰከርባቸው ነው


የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ
የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከተከሰሱበት የንግድ ሥራ ማጭበርበር ጋራ በተያያዘ የቀድሞ ጠበቃ እና ጉዳይ አስፈጻሚያቸው ማይክል ኮኸን ዋና ምስክር ሆነው ቃላቸውን ይሰጣሉ። ትራምፕ የተከሰሱበት የፍትሃብሔር ክስ በግዙፉ የትራምፕ የንግድ ተቋም ላይ የመፍረስ አደጋ ሊደቅን ይችላል ተብሏል።

የቅርብ አዋቂዎች እንደተናገሩት ትራምፕ በዛሬው ችሎት ይገኛሉ ተብሎም ተጠብቋል። አጋጣሚው ከአምስት አመት በፊት ከትራምፕ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ካቋረጡ በኋላ ከግንባር ቀደም ነቃፊዎቻቸው አንዱ ከሆኑት ኮኽን ጋር ፊት ለፊት የሚተያዩበት ውጥረት ሊከስት ይችላልም ተብሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2024 በሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ግንባር ቀደም የሪፐብሊካን ተፎካካሪ የሆኑት ትራምፕ ትላንት ሰኞ በኒውሃምሸር ክፍለ ግዛት እያደረጉ ከነበሩት የምርጫ ዘመቻ እንቅስቃሴ ነው ዛሬ ወደ ችሎቱ የሚያቀኑት።

ትራምፕ ከክሱ ጋር ስለሚመለከቱ ጉዳዮች እንዳይናገሩ በፍርድ ቤት የተሰጣቸውን ትእዛዝ በመጣሳቸው የ5000 ዶላር መቀጮ ጉዳዩን ባስቻሉት ዳኛ ከተበየነባቸው ቀናት በኋላ ችሎት ሲቀርቡ የመጀመሪያቸው መሆኑ ነው።

ዲሞክራቷ የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ ያቀረቡት ይህ ክስ ትራምፕ ከባንኮች የተሻለ የብድር ውል ለማግኘት የንብረቶቻቸውን ዋጋ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ከፍ አድርገው በመተመን የማጭበርበር ወንጀል ፈጽመዋል የሚል ነው።

በሌላ በኩል ኮኸን ራሳቸው የፈጸጸሙት የሕግ መተላለፍ በከሰተው ሁኔታ ውስጥ ሳሉ ከትራምፕ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ከማቋረጣቸው አስቀድሞ ለዓመታት የትራምፕ የግል ጠበቃ እና ጉዳይ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል። እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2019 የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ከትራምፕ የንግድ ሥራዎች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ምርመራ ባካሄደበት ወቅት ኮኸን የሰጡት ምስክርነት ለአቃቤ ሕግ ሌቲሽያ ጄምስ ክስ አቀጣጣይ ተደርጎ ታይቷል።

ትራምፕ ‘ሕግ የተላለፈ ድርጊት አልፈጸምኩም’ ሲሉ የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለው ”ለፖለቲካ አላማ ማስፈጸሚያ ሲባል የተቀነባበረ ነው” በሚል ውድቅ ማድረጋቸው ይታወሳል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG