ዋሺንግተን ዲሲ —
የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ቢል ክሊንተን በካሊፎኒያ ሆስፒታል ገብተው የህክምና እርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ማገገማቸውን ሀኪሞች ትናንት ሀሙስ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የ75 ዓመቱ ክሊንተን ባለፈው ማክሰኞ ምሽት ካሊፎኒያ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የገቡት ከኮቪድ-19 ውጭ ለሆነ ኢንፌክሽን ተጋልጠው በሆስፒታሉ የኧርቪን ሚድካል ሴንተር ህክምና ለማግኘት መሆኑን ቃል አቀባያቸው ኤንጀል ኡሬና በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡
ቃል አቀባይዋ አያይዘው “የሆስፒታሉ ሠራተኞች፣ ዶክተሮችና ነርሶች ላደረጉላቸው አስደናቂ እንክብካቤ ምስጋና ይግባውና፤ አሁን አገግመው በጥሩ መንፈስ ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡
ክሊንተን ወደ ሆስፒታል የተወሰዱት በተጫጫናቸው የድካም ስሜት ነው፡፡ ዶክተሮች በሽንት መተላለፊያ ኢንፌክሽን ምልክት መኖሩን ባደረጉት የደም ምርመራ ከተመለከቱ በኋላ ሆስፒታል ቆይተው ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ወስነዋል፡፡ በዚህም መሠረት ክሊንተን ለተከታታይ ህክምና ሆስፒታል እንደሚቆዩም ተነግሯል፡፡