የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፣ በባለቤታቸው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እና በራሳቸው ስም የተመሠረተው፣ የኃይለ ማርያም እና ሮማን ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ከመደበኛ ሥራቸው ውጭ ቤተሰባቸውንም የመምራት ድርብ ኃላፊነት ያለባቸው ወ/ሮ ሮማን፣ ከቤተ መንግሥት ከወጡም በኋላ፣ የሀገራቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመቅረፍ ሒደት፣ በፋውንዴሽኑ አማካይነት የበኩላቸውን ድርሻ በማበርከት አሻራቸውን እያኖሩ መቀጠልን እንደወደዱ ይናገራሉ፡፡
ፋውንዴሽኑ፥ በበጎ አድራጎት ሥራ ኅብረተሰቡን ማገዝ እንደሚገባ በማመን የተመሠረተ እንደኾነ የተናገሩት ወ/ሮ ሮማን፣ ጋምቤላን በማስቀደም በደቡባዊ እና ደቡባዊ ምዕራብ የአገሪቱ ክፍሎች መንቀሳቀስን መርጠዋል።
የአራት ዓመታትን ዕድሜ ያስቆጠረው ፋውንዴሽኑ፣ በአሁኑ ወቅት ትኩረቱን በሴቶች ላይ አድርጎ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡
“በተለይ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ በዱር እንስሳት እና በዕፀዋት የበለጸጉ የተፈጥሮ ፓርኮች አሏቸው፤ ነገር ግን እነዚያ አካባቢዎች ለቱሪስት መስሕብነት አልዋሉም፤” ያሉት ወ/ሮ ሮማን፣ በተፈጥሮ ፓርኮቹ ዙሪያ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች፣ በትምህርት እና በጤና መሠረተ ልማቶች ዕጦት፣ በጣም የተጎዱ እና ከመሀል ሀገር ጋራ ሲነጻጸሩ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡
ይህን ክፍተት ከወዲሁ መሙላት ካልተቻለ፣ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ከመሀል ሀገር ጋራ ያላቸው ልዩነት እየሰፋ ሊደርሱብት የማይቻል ይኾናል፤ በማለት ወ/ሮ ሮማን ያሳስባሉ።
በእነዚህ ጠረፋማ አካባቢዎች የሚከናወኑት የፋውንዴሽኑ የበጎ አድራጎት ተግባራት በዋናነት ሴቶችን ያማከሉ እንደኾኑም ተናግረዋል።
/ከወ/ሮ ሮማን ጋራ ቆይታ ያደረገው ኬኔዲ አባተ ነው፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/