ዋሺንግተን ዲሲ —
የረዥም ጊዜ የግብፅ መሪ የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ በ91 ዓመት ዕድሜያቸው አረፉ።
ማረፋቸው ዛሬ የተገለጸው በሀገሪቱ የመንግሥት ቴሌቪዥን ነው።
ሆስኒ ሙባረክ ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በግብፅ በተካሄደው ህዝባዊ አምፅ ከሥልጣን ከመወገዳችድው በፊት ሃገሪቱን ለ30 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ገዝተዋል።
በግብፁ አየር ኃይል ውስጥ በማገልገል እድገቶች ሲያገኙ ከቆዩ በኋላ በሂደት አዛዥና ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር ለመሆን በቁ።
እአአ በ1975 ዓ.ም የወቅቱ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳት ምክትል ሆነው ተሾሙ።
እአአ በ1981 ዓ.ም አንዋር ሳዳት በእስላማዊ አማጽያን ሲገደሉ ሙባረክ ከጎናቸው ነበሩ።
ከዚያም የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው እአአ በ1979 ዓ.ም ከእስራኤል ጋር የተፈረመውን የሰላም ውል በማክበር ታማኝ የምዕራብ ሃገሮች ወዳጅ ሆነው በሥልጣን ለማቆየት ቻሉ። አብዛኞቹ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገሮች ከእስራኤል ጋር የተደረገውን የሰላም ሥምምነት አጥብቀው ይቃወሙ እንደነበር የሚታወቅ ነው። ሙባረክ ግብፅን ረግጠው በመግዛት ይታወሳሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አገዛዝ በማወጅ የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱና መሰረታዊ ነፃነቶችን እንዲገድቡ ሙሉ ሥልጣን ተሰጣቸው።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ