በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሞርሲ ቀብር ተፈፀመ


ፎቶ ፋይል፡- የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሞርሲ
ፎቶ ፋይል፡- የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሞርሲ

ትናንት ያረፉት የቀድሞ የግብፅ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሞርሲ ቀብር ተፈፀመ።

በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት እና በኋላ ከሥልጣናቸው የተወገዱት ሞርሲ ትናንት ካይሮ ፍርድ ቤት ችሎት ፊት ቀርበው፣ ራሳቸውን ስተው ነው በዚያው ህይወታቸው ያለፈው።

ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ካይሮ ቶራ ወህኒ ቤት ውስጥ በሚገኘው መስጂድ ፀሎት ከተካሄደላቸው በኋላ በመዲናዋ ናስር ወረዳ በሚገኝ መካነ መቃብር ቀብራቸው መከናወኑን የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጠበቆች አንዱ ገልፀዋል።

ወንድ ልጃቸው አህመድ ሲናገሩ አባታችንን ሻርኪያ ክፍለ ሃገር በሚገኘው የቤተሰብ መቃብር እንዳናሳርፈው በመንግሥት ፀጥታ ክፍል ተከልክለናል ብለዋል።

የስድሳ ሰባት ዓመቱ ሞሃመድ ሞርሲ በተመሰረተባቸው የመንግሥታዊ ሥለላ ክስ ለችሎቱ ለአምስት ደቂቃ ያህል ከተናገሩ በኋላ ጥቂት ደቂቃዎች ቆይተው ተዝለፍልፈው መውደቃቸው ነው የተነገረው።

ወደሆስፒታል መወሰዳቸውን የገለፀው የመንግሥቱ ቴለቭዢን ነገር ግን የደረሱት በልብ ድካም ምክንያት ህይወታቸው አልፎ ነው ሲል አስረድቷል።

የሙስሊም ወንድማማችነት ቡድን የነፃነት እና የፍትህ ፖለቲካ ፓርቲ ባወጣው መግለጫ ሞርሲን መድሃኒት እንዳያገኙ በመከልከል እና መጥፎ ምግብ በመስጠት ሆን ብለው ቀስ በቀስ የገደሉዋቸው የሃገሪቱ ባለሥልጣናት ተጠያቂዎች ናቸው ብሉዋል። ቡድኑ በድረ ገፁ ባወጣው መግለጫው ህዝቡ በቀብራቸው እና በዓለም ዙሪያ ባሉ የግብፅ ኤምባሲዎች እንዲሰባሰብ ጥሪ አቅርቧል።

አምነስቲ ኢንተርናሺናል የግብፁ ባለሥልጣናት ስለቀድሞው ፕሬዚዳንት አሟሟት ከወገንተኝነት ነፃ ምርመራ እንዲያካሂድ አሳስበዋል። የተመድ የሰብዓዊ መብት ቢሮም ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቋል።

የግብፁ ዋና አቃቤ ህግ የአሰከሬን ምርመራ ይካሄዳል ብለዋል፡፡

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG