በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ የእርሻ መሬቶችና "የምግብ ዋስትና"


Food Security in Africa and Land Grab Issue Discussion, Washington D.C. (Mobile Foto)
Food Security in Africa and Land Grab Issue Discussion, Washington D.C. (Mobile Foto)

የአፍሪካ መሬቶች በውጭ ሰዎችና ኩባንያዎች በሽያጭ ወይም በኪራይ ወይም በ"መሬት ቅርምት" መያዛቸው አስግቷል፡፡

በአፍሪካ እየታየ ያለው የውጭ ሃገሮች እያካሄዱ ያሉት መሬት የመቀራመት ዘመቻ ሃገሮቹ አስመዝግበናል የሚሉት የኢኮኖሚ ዕድገት የሃሰት ቁጥሮች እንዲያሣይ አስተዋፅዖ ያበረክታል ሲሉ አንድ አፍሪካዊ ተመራማሪ ገለፁ፡፡

የመሬት መቀራመት ዘመቻው ለአፍሪካ የደህንነትም አደጋ ነው የሚሉ ተሣታፊዎች የተገኙበት "የምግብ ዋስትናና መሬትን መቀራመት" በሚል ርዕስ የተሰየመ ስብሰባ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ ተካሂዷል፡፡

ከዘመኑ የአፍሪካ ግብርና ነክ ጉዳዮች ቀደም ያለ ሥፍራከያዙትና ብዙም ከሚነገርላቸው መካከል ተቺዎቹና ተቃዋሚዎቹ "መሬት መቀራመት" እያሉ የሚጠሩት፣ ሰጭና ተቀባይ ደግሞ በዓለም ባንክም አጠራር "ኪራይ፣ ወይም ግዥ ወይም ስጦታ" የሚሉት ዘመነኛው የውጭ ሃገሮች ወደ አፍሪካ ሃገሮች እየዘለቁ የሚይዙት የመሬት አስተዳደር ዘይቤ ነው፡፡

ይህ የ"መሬት መቀራመት" ጉዳይ የአፍሪካን ሃገሮች ወደባሰ ድኅነት ከትቶ የበረታ መዘዝ ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ፖል ማቲው የተባሉ የዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት (ኤፍኤኦ) ባለሥልጣን ሰሞኑን ካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ላይ አስጠንቅቀዋል፡፡

በድኅነቱ ላይ ማኅበራዊ ውጥረትን ሊያባብስ እንደሚችልም የኤፍኤኦው የአየር ንብረት፣ የኢነርጂና የመሬት ክፍፍል ከፍተኛ መኮንን ፖል ማቲው ጠቁመው የአፍሪካ ሃገሮች ከያዙት መሬታቸውን የማቀራመት ሩጫ እንዲቆጠቡ አሣስበዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ አምስት የአፍሪካ ሃገሮች ውስጥ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ከ2004 ዓ.ም ወዲህ ባሉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ቢያንስ 2.5 ሚሊየን ሄክታር፣ ወይም 25 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ወይም 23 ቢሊየን ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ቦታ በዙ ሃብት ላላቸው ነዋይ አፍሳሾች ተሰጥቷል፡፡

ዓለምአቀፉ የረድዔት ድርጅት አክሽንኤድ ደግሞ የአፍሪካ ሃገሮችን ታላላቅ የመሬት ኪራይ ስምምነቶችን ከመፈረም እንዲያስቆማቸው የዓለሙን የምግብና የግብርና ድርጅት ኤፍኤኦ ጠይቋል፡፡

አክሽንኤድ በመግለጫው ኩባንያዎች፣ ባለነዋዮች፣ በሃገሮች የሚደገፉ የገንዘብ አፍሣሽ ድርጅቶች ብዙውን ጊዜ የድኃ ሕዝቦችን ሕይወት ሊፈታተን በሚችልና የሃገሮቹንም ምጣኔ ኃብት በሚያዳክም ሁኔታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ባሕርና ድንበር እየዘለሉ የእንግሊዝን ስፋት እጥፍ የሚያክል መሬት (ወደ ሃምሣ ሚሊየን ሄክታር ማለት ነው) ወስደዋል፡፡

ስለዚህ በኢትዮጵያ፣ በጋና፣ በማሊ፣ በማዳጋስካርና በሱዳን እየተካሄደ ስላለው ሰፊ "የመሬት መቀራመት" የሚናገረው የመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም የምግብና የግብርና ድርጅት (ኤፍኤኦ) ወይም አክሽንኤድ ብቻ አይደሉም፡፡ በእነዚህ ሃገሮች ውስጥ "የመሬቱን መቀራመት" አስመልክቶ ጥናት ያካሄደው የኦክላንድ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አኑሪታ ሚታል እነዚያን ለውጭ የተሰጡ መሬቶች የሰጡ ሃገሮች ሰዎችን እንደበዪ ተመልካች እንደሚመለከቷቸው በቅርቡ ለአሜሪካ ድምፅ ሰጥተውት በነበረ ቃለ ምልልስ ተናግረው ነበር፡፡

የወቅቱ ቋሚ አጀንዳ የሆነው "የመሬት ቅርምት" ባለፈው ሣምንትም ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ እንዲሁ የመነጋገሪያ አጀንዳ ነበር፡፡

ይህ የዓለም ባንክ እንደሚደግፈው የሚነገረው የመሬት መቀራመት ጉዳይም እንዲሁ በብዙ ሃገሮች የተገኙ ተሣታፊዎች የተገኙበት የፖሊሲ ጥናቶች ኢንስቲትዩት ያዘጋጀው "የምግብ ዋስትናና የመሬት ቅርምት በአፍሪካ" በተሰኘ ርዕስ የተካሄደ የውይይት መድረክም ርዕስ ነበር፡፡

የአሜሪካ ድምፁ ሰሎሞን አባተ በስብሰባው ላይ ተገኝቶ አንዳንድ ተሣታፊዎቹንም አነጋግሮ ያጠናቀረውን ዘገባ ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG