በህዳር ወር ኢንዶኔዥያ ባሊ ውስጥ በሚካሄደው የቡድን ሃያ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ቀደም ሲል አንገኝም ብለው የነበሩት ምዕራባውያን መሪዎች በጉባዔው ላይ እንደሚካፈሉ ፍንጭ እየሰጡ ናቸው። የሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን በርቀት በኢንተርኔት አማካይነት ሊሳተፉ ይችሉ ይሆናል ሲል ክሬምሊን ቤተ መንግሥት ገልጿል።
ትናንት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል የፑቲንን በጉባኤው ላይ በአካል ይሳተፉ እንደሆን "በአስፈላጊው ሰዓት እንወስናለን" ብለዋል።
አስተናጋጇ ሀገር ኢንዶኔዥያ ፑቲንን እንዳይሳተፉ እንድትከለክል ምዕራብ ሀገሮች ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል። በመሆኑም ፑቲን በአካል ሳይሆን በርቀት በቪዲዮ ቢካፈሉላት ከከረመችበት የዲፕሎማሲ ራስ ምታት ሊገላግላት ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ ሌሎችም የቡድን ሰባት መሪዎች ፑቲን የሚመጡ ከሆነ አንገኝም ብለው እንደነበር ይታወሳል።
የዘንድሮ የቡድን ሃያ ሊቀ መንበር የኢንዶኔዥያ ፕሬዚዳንት ጆኮ ዊዶዶ ጉባኤው እንዳይሰናከል ዲፕሎማሲያው ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ዊዶድ ረቡዕ ወደ ኪቭ ተጉዘው ከዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን ባለፈው ሳምንት ደግሞ በጀርመን ከቡድን ሰባት መሪዎች ጋር ተገናኝተዋል። ትናንት ደግሞ በሞስኮ ከሩሲያ ፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ተነጋግረዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር በጉባኤው ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁ ሲሆን ሌሎቹም የቡድን ሰባት ሀገሮች ሩሲያ ከቡድን 20 አባልነት ባትሰረዝም ጉባኤው ላይ ይገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ጠቅሰዋል። ፕሬዚዳንት ባይደን ይገኙ እንደሆን ቪኦኤ ኋይት ሀውስን የጠየቀ ሲሆን ለጊዜው ምላሽ አላገኘም።