በናይጄሪያ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ምክንያት ቢያንስ 49 ሰዎች ሲሞቱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የሀገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ባለስልጣን ዛሬ ሰኞ አስታውቋል።
በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በጎርፍ አደጋው ክፉኛ በተጠቁት ጂጋዋ፣ አዳማዋ እና ታራባ ግዛቶች ውስጥ 41 ሺህ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውንም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ማንዞ ህዝቅዔል ተናግረዋል።
ባለፈው አመት በናይጄሪያ ከአስር አመት በላይ ጊዜ ውስጥ ታይቶ የማያውቅ አስከፊ የጎርፍ አደጋ ደርሶ ከ600 በላይ ሰዎችን ሲገድል፣ 1.4 ሚሊየን ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሎ ነበር። 440 ሺህ ሄክትር የእርሻ መሬትም ወድሟል።
የብሔራዊ አደጋ ጊዜ ባለስልጣኑ ለሮይተርስ ሲናገሩ "በተለይ በሰሜኑ አካባቢ የዝናብ ወቅቱ ከፍ ወደሚልበት ግዜ እየገባን ነው በመሆኑ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው" ብለዋል።
የጎርፍ አደጋው ወደ 693 ሄክታር የሚጠጋ የእርሻ መሬት ላይ ያሉ ሰብሎችን አውድሟል። ባለሁለት አሃዝ የዋጋ ንረትን እየተዋጋች ያለችው ናይጄሪያ ከፍተኛ የምግብ ዋጋም እየታመሰች ነው።
በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ ታጣቂዎች በሚያደርሱት ጥቃት ሳቢያ አርሶ አደሮች እርሻቸውን ጥለው እየተሰደዱ ባሉበት ወቅት፣ በከፍተኛ ሁኔታ እየጣለ ያለው ዝናብ በግብርናው ላይ ተጨማሪ ጉዳት እያደረሰ መሆኑም ተገልጿል።
መድረክ / ፎረም