በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጎርፍ አደጋ በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ጉዳት ማድረሱን ኦቻ አስታወቀ


ፎቶ ፋይል፦ ጋምቤላ
ፎቶ ፋይል፦ ጋምቤላ

በጋምቤላ ክልል፣ ባለፈው የክረምት ወቅት በጣለው ዝናም፣ የባሮ እና ጊሎ ወንዞች ከወሰናቸው አልፈው በመፍሰሳቸው፣ ለጎርፍ ተጋላጭ በኾኑ አካባቢዎች ጉዳት እንዳደረሱ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ(UN-OCHA) አስታወቀ።

በአኝዋክ እና ኑዌር ዞኖች፣ እንዲሁም በኢታንግ ልዩ ወረዳ ውስጥ፣ ከ52ሺሕ300 በላይ ሰዎች እንደተጎዱ፣ ከ37ሺሕ በላይ የኾኑቱ ደግሞ እንደተፈናቀሉ፣ የማስተባበርያ ቢሮው ገልጿል፡፡

በክልሉ ከታረሰው 141ሺሕ ሄክታር ሰብል፣ ከ8ሺሕ700 ሄክታር በላይ የሚኾነው በጎርፉ ጉዳት እንደደረሰበት፤ ከአንድ ሺሕ በላይ የቀንድ ከብቶች እንደሞቱ፤ ፍየሎችን፣ በጎችንና ዶሮዎችን ጨምሮ ከ21ሺሕ700 በላይ እንስሳትም፣ በከብት በሽታዎች እንደተጠቁ፣ ሪፖርቱ አመልክቷል።

በጋምቤላ ክልል፣ በየዓመቱ ከሐምሌ እስከ መስከረም ባሉት የክረምት ወራት፣ ጎርፍ በተደጋጋሚ የሚከሠት ሲኾን፣ በርካታ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ይፈናቀላሉ።

በኦቻ ሪፖርት መሠረት፣ በዚኽ ዓመት ጎርፍ፣ ሁለት ጤና ጣቢያዎች እና 24 የጤና ኬላዎች አገልግሎት መስጠት ሲያቆሙ፣ 90 ትምህርት ቤቶችም በከፊል በመጎዳታቸው፣ የ63ሺሕ ተማሪዎችን የመማር ማስተማር ሒደት አስተጓጉሏል።

የማስተባበሪያ ቢሮው አክሎ እንዳመለከተው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተጎጂዎች፣ 317 ሜትሪክ ቶን ስንዴ እና 169 ሜትሪክ ቶን ዱቄት አከፋፍሏል። ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ተቋማትም፣ ለ140ሺሕ ተማሪዎች፣ ምግብ ነክ ያልኾኑ ቁሳቁሶችንና የትምህርት መሣሪያዎችን ለማቅረብ ቃል ገብተዋል።

ኦቻ በሪፖርቱ እንዳስታወቀው፣ በአሁኑ ሰዓት ዋና ፍላጎት እንደኾኑ የተጠቀሱት፥ ምግብ፣ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እና የትምህርት መሣሪያዎች ናቸው።

በተመሳሳይ ኹኔታ፣ ጥቅምት 18 እና 19 ቀን፣ በሶማሌ ክልል በዘነመው ዝናም ምክንያት፣ የ12 ሰዎች እና 2ሺሕ200 እንስሳት ሕይወት አልፏል። በ15ሺሕ500 አባወራዎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲኾን፣ 2ሺሕ200 የሚኾኑቱ ደግሞ ተፈናቅለዋል። ጎርፉ ጉዳት ያደረሰባቸው አካባቢዎች፥ አፍዴር፣ ጃራር፣ ሊባን፣ ኖጎብ እና ሸበሌ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 42 አካባቢዎች ናቸው፡፡

የደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች በኾኑት ጋሞ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ እና ወላይታ ዞኖችም፣ ከፍተኛ የዝናም መጠን እንደተመዘገበ ያመለከተው የኦቻ ሪፖርት፣ በተለይ ጥቅምት 18 ቀን በዘነመው ከፍተኛ ዝናም፣ በጋሞ የሚኖሩ 1ሺሕ200 ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG