በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ላሊበላ እና ጎንደር የሚያደርገውን በረራ አቋረጠ


ፎቶ ፋይል፦ ላሊበላ ከተማ
ፎቶ ፋይል፦ ላሊበላ ከተማ

· “ፋኖ የላሊበላን አየር ማረፊያ ተቆጣጥሯል”- የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ቢሮ

የኢትዮጵያው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በዐማራ ክልል እየተባባሰ የመጣው ሁከት እንዳሳሰባቸው መግለጻቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ወደ ክልሉ የሚያደርገውን በረራ ማቋረጡን አስታውቋል።

የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ አሸናፊ ዘርዓይ፣ “ወደ ጎንደር እና ላሊበላ የሚደርገው በረራ ተቋርጧል፤” ሲሉ፣ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

በፌዴራሉ የመከላከያ ኀይል እና በዐማራ ክልል በሚገኙ የፋኖ ታጣቂዎች መካከል እየተካሔደ በሚገኘው ግጭት ምክንያት፣ እንግሊዝ እና ስፔን፣ ለዜጎቻቸው የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሲያወጡ፣ የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ቢሮ፣ “የዐማራ ሚሊሻ ፋኖ፣ የላሊበላን አየር ማረፊያ ተቆጣጥሯል፤” ሲል አስታውቋል።

የዩኔስኮ ቅርስ ኾነው የተመዘገቡ አብያተ ክርስቲያናት ባሉባት ላሊበላ ከተማ፣ በአየር ማረፊያው የሚደረገው በረራ ማክሰኞ ዕለት እንደተቋረጠ፣ የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር፣ የክልል ልዩ ኃይሎች ወደ ፌዴራሉ ጦር እንዲቀላቀሉ የዘረጋውን ፕሮግራም እና አፈጻጸሙን ተከትሎ፣ በዐማራ ክልል ያሉ ኃይሎች፣ “ውሳኔው፥ ክልሉን ያዳክማል፤” በሚል ተቃውመውታል።

“በዐማራ ክልል በልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚታዩ የጸጥታ ችግሮች፣ አሳሳቢ እየኾኑ መጥተዋል፤” ሲሉ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ ትላንት በፌስቡክ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

“ሰላም ከሌለህ ሁሉን ታጣለኽ' የሚባለውን እውነታ ከልብ በማጤን፣ በአስተውሎት መጓዝ በሚገባን ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፤” ሲሉ አክለዋል።

“ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው፣ ያላረኩንና ሌሎችም ችግሮች እና ስሜቶች ይኖራሉ፤” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “ለእነዚኽ ጉዳዮች፣ ቆም ብለን በማሰብ፣ በሰላሙ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፤” ሲሉ አክለዋል።

የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ “ለሁከቱ ሓላፊነቱን የሚወስዱት የፋኖ ታጣቂ ነን የሚሉት ተዋጊዎች ናቸው፤” ሲሉ፣ የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ፣ በዚኽ ሳምንት በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱትን ኀይሎች ያወገዙት ኮሎኔሉ፣ ሠራዊታቸውን በሚያጠቁ ወይም ጥቃቱን በሚያመቻቹ ኀይሎች ላይ ርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል።

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ፣ ዜጎቹ፥ ወደ ዐማራ ክልል እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል። “የፋኖ ሚሊሺያ፥ በቅርቡ፣ የላሊበላን አየር ማረፊያ ተቆጣጥሯል፤” በማለት ገልጿል።

ኤኤፍፒ ያነጋገረው የላሊበላ ነዋሪ፣ አየር ማረፊያው፣ በፋኖ ቁጥጥ ሥር እንደኾነ ተናግሯል። በላሊበላ ከተማ ዳርቻም ውጊያ መኖሩን የተናገረው ይኸው ነዋሪ፣ “ወደ ከተማው የሚያስገባውን መንገድ፣ ፋኖ ዘግቶታል፤” ሲል አክሏል።

ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ጋራ ተመሳሳይ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ያወጣው፣ በዐዲስ አበባ የሚገኘው የስፔን ኤምባሲ፣ ላሊበላ የሚገኙ የስፔን ዜጎች፣ ኤምባሲውን እንዲያነጋግሩ፣ ቀድሞ ቲዊተር በመባል በሚታወቀው “X” ማኅበራዊ መድረክ ላይ አስታውቋል።

የዐማራ ክልል ኀይሎች እና የአካባቢ ሚሊሻዎች፣ የፌዴራሉ ጦር፣ ለሁለት ዓመታት ከትግራይ ኀይሎች ጋራ ባደረገው ጦርነት፣ የፌዴራሉን ጦር ወግነው ተሰልፈው ነበር። በጥቅምት 2015 የተፈረመው የሰላም ስምምነት፣ የዐማራ ኀይሎችን አስከፍቷል፤ ያለው የኤኤፍፒ ዘገባ፣ ስምምነት ቢደረግም፣ የዐማራ ልዩ ኃይል እና ፋኖ፣ ምዕራብ ትግራይን መቆጣጠር መቀጠላቸውን አመልክቷል።

“የክልል ኀይሎች ፈርሰው ወደ ፌዴራል የጸጥታ ተቋማት መቀላቀላቸው፣ ብዝኀነት ያለበትን የኢትዮጵያ አንድነት ያጠናክራል፤” ሲሉ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ባለፈው ሚያዝያ ወር መናገራቸውን፣ የኤኤፍፒ ሪፖርት አስታውሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG