በፍሎሪዳ ግዛት የተወዳደሩት ዲሞክራቱ ማክስዌል አሌሃንድሮ ፍሮስት ተቀናቃኛቸውን ሪፐብሊካኑን ካልቪን ዊምቢሽን በማሸነፍ በያዝነው ሚሊንየም መዳረሻ እና ከዛ ወዲህ የተወለዱ የመጀመሪያው የምክር ቤት አባል ሆነዋል።
የ25 አመቱ ፍሮስት የጠመንጃ ህግ ማሻሻያ እና የማኅበራዊ ፍትህ ተሟጋች ሲሆኑ በአብዛኛው የዲሞክራት መራጮች በሚገኙበት ኦርላንዶ አካባቢ ነው የተወዳደሩት።
ዛሬ ማክሰኞ በተደረገው ድምፅ አሰጣጥ ፍሎሪዳን ወክለው ቢያንስ ስድስት ተመራጮች የዩናይትድ ስቴትሱን ምክር ቤት የሚቀላቀሉ ሲሆን ፍሮስት ከነሱ አንዱ ነው። ሪፐብሊካኖች የምክር ቤቱን አብላጫ ድምፅ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ሲሆን አገረገዢው ሮን ደሳንተስ ድል በመጎናፀፍ ቀዳሚ ሆነዋል።
ፍሮስት ጠንከር ያለ የጠመንጃ ቁጥጥር ህጎችን የሚጠይቀውን "ለህይወታችን እንሰለፍ" የተሰኘውን ሰልፍ አዘጋጅ ሲሆኑ በፅንስ ማቋረጥ መብት ላይ የሚደረጉ ክልከላዎች ዙሪያም ተቃውሞዋቸውንአሰምተዋል።
'ዚ' ትውልድ በመባል የሚጠሩት እአአ በ1990ዎቹ መጨረሻ እና በሁለት ሺህ አስራዎቹ የተወለዱ ሲሆኑ አንድ ሰው ለምክር ቤት አባልነት ለመወዳደርም ሆነ ለመመረጥ ቢያንስ 25 አመት ሊሞላው ይገባል።
ተፎካካሪያቸው የነበሩት የ72 አመቱ ዊምቢሽ እራሳቸውን 'ክርሲያን፣ ወግ አጥባቂ እና ህገ-መንግሥታዊ እጩ' ብለው የሚጠሩ የቀድሞ ሰራዊት አባል ናቸው።
ባለፈው ምርጫ ፍሎሪዳን የወከሉ 16 ሪፐብሊካኖች በምክር ቤቱ መቀመጫ የነበራቸው ሲሆን ዲሞክራቶች ደግሞ 11 ነበሩ። አጠቃላይ 27 መቀመጫዎች የነበራት ፍሎሪዳ በህዝብ ቁጥሯ መጨመር ምክንያት አንድ ተጨማሪ መቀመጫ በማግኘቷ አሁን 28 የምክርቤት መቀመጫዎች አሏት።
በተያያዘ ዜና በፍሎሪዳ ተመራጭ የነበሩት ዲሞክራቷ ስቴፈኒ መርፊ፣ በመሀል ፍሎሪዳ የሚገኘው የመወዳደሪያ ወረዳቸው ድጋፍ በአብላጫው ወደሪፐብሊካን በማድላቱ በድጋሚ ለምርጫ ላለመወዳደር ወስነዋል።
በደቡብ ፍሎሪዳ ደግሞ ዶሞክራቱ ቴድ ዶይች ጡረታ መውጣታቸውን በመግለፃቸው ሊተካቸው ለሚችል ዲሞክራት እድል ከፍቷል።
በሥልጣን ላይ ሆነው በድጋሚ ከሚወዳደሩ መካከል በማያሚ የሚደረገው ውድድር በጣም የተቀራረበ ሲሆን አካባቢው በዲሞክራቶች እና በሪፐብሊካኖች መካከል የመቀያየር ታሪክ ያለው ነው
ለአብዛኞቹ የፍሎሪዳ መራጮች ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስባቸውሲሆን አሶስዬትድ ፕሬስ ካሰባሰበው አስተያየት ሦስት አራተኛ የሚሆኑት በሀገሩቱ ያሉ ነገሮች ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እየሄዱ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተመልክቷል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት ግማሹ ኢኮኖሚውና የሥራ እድል የሀገሪቱ አንገብጋቢ ጉዳዮች ናቸው ብለው እንደሚያምኑም ተናግረዋል።