የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ባለሥልጣናት ከዩናይትድ ስቴትስ የተላኩት የኤምፖክስ 50 ሺህ ክትባቶች ከዩናይትድ ስቴትስ መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ዛሬ ማክሰኞ ከዩናይትድ ስቴትስ የተላኩት በቀድሞ ስሙ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ክትባቶች ኮንጎ የደረሱት ከአውሮፓ ህብረት የተላኩት የመጀመሪያዎቹ ክትባቶች ከደረሱ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
በበሽታው በጣም በተጎዱት ኤኩዊተር፥ ደቡባዊ ኪቩ እና ሳንኩሩ በተባሉት ሦስት አውራጃዎች የሚኖሩ አዋቂዎች ከመጭው የጎርጎርሳዊያኑ ጥቅምት ሁለት አንስቶ በቅድሚያ መከተብ እንደሚጀምሩ የዴሞክራቲክ ሪፐሊክ ኮንጎ የኤም ፖክስ ምላሽ ኮሚቴ አስተባባሪ ክሪስ ካኪታ ኦሳኮ አስታውቀዋል፡፡
በአውሮፓ ህብረት ተልከው ባለፈው ሳምንት ኪንሻሳ የደረሱት መቶ ሺህ ክትባቶች በዴንማርኩ ኩባኒያ ባቫሪያን ኖርዲክ የተመረቱ ጄይኒዮስ የተባሉ ክትባቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ከዩናይትድ ስቴትስ የተላኩት 50 ሺህ ክትባቶችም የጄይኒዮስ ክትባቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ተጨማሪ 100 ሺህ ክትባቶች ወደኮንጎ ተልከዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የጤና ሥጋት የጋረጠው የዴሞክራቲክ ኮንጎ ኤምፖክስ ወረርሽኝን በቁጥጥር ስር ለማዋል 250 ሺህ ክትባቶች ከሚያስፈልጉት ከሦስት ሚሊየን ክትባቶች አንጻር ኢምንት ናቸው ሲሉ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተጨማሪ 500 ሺህ ክትባቶችን ለመለገስ ቃል ቢገቡም፤ ክትባቶቹ ወደ ኮንጎ የሚደርሱበት ጊዜ ግን አልታወቀም፡፡
መድረክ / ፎረም