በሎንግ አይላንድ፣ ኒው ዮርክ ቅዳሜ ዕለት ተከስቶ የነበረው የዱር እሳት በቁጥጥር ሥር ቢውልም፣ በሥፍራው የሚታየው ጠንካራ ነፋስ አካባቢውን አኹንም ለእሳት ተጋላጭ ሊያደርገው እንደሚችል ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ቅዳሜ ዕለት በሎንግ አይላንድ አራት ሥፍራዎች እሳት ከተስቶ አውራ ጎዳናዎችንና በአካባቢው የሚገኘውን ወታደራዊ ሠፈር እንዲዘጋ ማስገደዱን ተከትሎ፣ የግዛቲቱ መሪ ካቲ ሆቹል የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ አውጀዋል።
በዐይን ሊታይ የሚችለው እሳት ሁሉ እንደጠፋና፣ በነፋስ አማካይነት ወደ ሌላ ሥፍራ እንዳይስፋፋ የእሳት አደጋ ሠራተኞች ዙሪያውን እንደተቆጣጠሩ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ትላንት እሑድ የነፋሱ ፍጥነት በሰዓት 48 ኪሎ ሜትር ስለነበር ስጋት ቢፈጠርም፣ አዲስ የተስፋፋ እሳት እንዳልነበር ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ሁለት የእሳት አደጋ ሠራተኞች ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ሕክምና እንዳገኙም ታውቋል።
የእሳቱ መንስኤ በመመርመር ላይ እንደሆነም የአሶስዬትድ ፕረስ ዘገባ አመልክቷል። መርማሪዎች 911 የአደጋ ጥሪ የደወሉ ሰዎችን በማነጋገርና በድሮን አማካይነትም አካባቢውን እያሰሱ እንደሆነ ተመልክቷል።
ሆን ተብሉ የተነሳ እሳት እንደኾነም ለማወቅ የሚመለከታቸው ባለሞያዎች ምርመራ ጀምረዋል።
መድረክ / ፎረም