“ብዙ ኩባኖች ተወዳጅ፤ በብዙ ኩባኖች የሚጠሉ” የነበሩት ፊደል ካስትሮ ያረፉት በዘጠና ዓመታቸው ነው።
በዋና ከተማ ሃቫና በታወቀው የአብዮት አደባባይ ዛሬ ሰኞ ብዛት ያለው ህዝብ ተሰባስቧል።
“ሁሉን ባደረገልን ሰው ህልፈት ያልተነካ ማን ይኖራል?” ያሉት ሆዜ ሉዊስ ሄሬራ “የኔንም፣ የልጆቼንም ህይወት የመሩ፤ እንደ ፈጣሪዬ ማለት ናቸው፡፡” ሲሉ ሃዘናቸውን ገልፀዋል።
ነጭ ለባሾቹ ሴቶች “ሌዲስ ኢን ዋይት” የተባለው የካስትሮ ተቃዋሚ ስብስብ መሪ በርታ ሶሌር በበኩላቸው
“በሰው ሞት አንደሰትም፡፡ … ሠብዓዊ ፍጡር ሲሞት ማለት ነው። ነገር ግን አምባገነኖች ሲሞቱ ደስ ይለናል።” ብለዋል።
ፊደል ካስትሮ የሞቱት ለረጅም ጊዜ ታመው የነበረ ሲሆን የህልፈታችው ምንነት ግን በይፋ አልተገለፀም።
በመላ ደሴቲቱ የሀገሪቱ ባንዲራ ዝቅ ተደርጎ እየተውለበለበ ነው።
ወጣቱ አብዮታዊ መሪ ፊደል እና ተዋጊዎቻቸው ከሲየራ ማዬስትራ ተራሮች ወደ ሃቫና ገስግሰው እ.ኤ.አ. በ1959 ዓ.ም. መንግሥቱን የተቆጣጠሩት ከበስተምሥራቁ እንደነበር ሲታወስ ከነገ ወዲያ ረቡዕ ጀምሮም የሙዋቹ አስከሬን አመድ ለሶስት ቀናት በዚያው አንፃር በስተምስራቅ አቅጣጫ በአጀብ ይጓዛል።
እ.ኤ.አ. ታህሳስ አራት ቀን የቀብራቸው ሥነ ስርዓት በደቡብ ምስራቅዋ ሳንቲየጎ ደ ኪዩባ ሳንታ ኢፍጌኒያ ይፈፀማል።
ትናንት በማያሚ ፍሎሪዳ ሌዲስ ኢን ዋይት የተባለው ስብስብስ አባላት ከሌሎች የካስትሮ ተቃዋሚ ቡድኖች ጋር ሆነው በኪዩባ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ለማሣሰብ የፊታችን ራቡዕ በአንድነት ትዕይንተ ህዝብ ለማድረግ ጥሪ አቅርበዋል።