ያለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን የብር ሜዳልያ አሸናፊው ፈይሣ ሌሊሳ ወደ ሃገሩ ገባ።
አትሌት ፈይሣን ቦሌ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው የተቀበሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ ናቸው።
ፈይሣ በወቅቱ በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ይደርስ የነበረውን የመብቶች ረገጣ በመቃወም ውድድሩን ሲጨርስ እጆቹን ወደላይ አመሣቅሎ የወቅቱ የምሬት መግለጫ የነበረውን “ይበቃል” ምልክት በኦሊምፒክ አደባባይ ላይ ካሣየ በኋላ ወደ ሃገሩ ሳይመለስ እንደወጣ በዚያው መቅረቱ ይታወቃል።
ከዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር አይሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው ለፈይሣ አቀባበል ካደረጉለት መካከል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስና የአትሌቲክስ ፌደሬሽን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌ/ኮ ደራርቱ ቱሉ ይገኙበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሣምንት አጋማሽ በተጠናቀቀው የቡየኖስ አይረስ የዓለም ወጣቶች ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ የተሣተፈው የኢትዮጵያ አትሌቶች ቡድን የደመቀ አቀባበል ተደርጎለታል።
ኢትዮጵያ 11 አትሌቶችን በሩጫና በቢስክሌት አሠልፋ ቡድኗ ስምንት ሜዳልያዎችን ይዞ ተመልሷል።
ሁለት የወርቅ፣ ሁለት የብርና አራት የነኀስ ሜዳልያዎችን ያሸነፈው ይህ የኢትዮጵያ ወጣቶች የኦሊምፒክ ቡድን የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንደተበረከተለትም ታውቋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ