በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩክሬን ጦር ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል እየተፋለሙ ነው


በዩክሬን ሠራዊት ውስጥ የሚገኙ ሴት ወታደሮች በወታደራዊ ትርኢት ልምምድ ወቅት ኬየቭ፣ እኤአ ሐምሌ 2/ 2021 በዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ከተለቀቀ ምስል የተወሰደ፣ ኦስሼይትድ ፕሬስ
በዩክሬን ሠራዊት ውስጥ የሚገኙ ሴት ወታደሮች በወታደራዊ ትርኢት ልምምድ ወቅት ኬየቭ፣ እኤአ ሐምሌ 2/ 2021 በዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ከተለቀቀ ምስል የተወሰደ፣ ኦስሼይትድ ፕሬስ

እንደ ዩክሬን መከላከያ ሠራዊት አገላለጽ፣ የሴት ወታደሮችና መኮንኖች ከዩክሬን ተዋጊ ጦር 15 ከመቶ የሚሆነውን እጅ ይሸፍናሉ፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2014 ጀምሮ ከ30ሺ በላይ ዩክሬናውያን ሴቶችም፣ ተዋጊ አርበኞች ሆነዋል፡፡

እነዚያ ቁጥሮች ከሩሲያ ወረራ ወዲህ ደግሞ እጅግ በጣም ጨምረዋል፡፡

ከእለታት በአንዱ የዩክሬን ጦርነት ቀን በኪዮቭ አስተርጓሚ ሆና ብቅ ያለችው ኤቭጌንያ ኤርማልድ ዕጩ ሌፍተናት ሆነች፡፡ ከዚያም የዩክሬን ድንበር አስከባሪ፣ ከዚያም በመቀጠል በዩክሬን ሠራዊት ውስጥ የአንድ ልዩ ጦር መኮንን ከመሆን ደርሳለች፡፡

ኤቭጌንያ ወደ ሠራዊቱ የገባችበትን ምክንያትና መንገድ እንደሚከተለው ትገልጸዋለች፦

“ሠራዊቱን መቀላቀል የፈለግኩት ዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸም በተጀመረበት እኤአ በ2014 ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያኔ በጣም ህጻን ልጅ ነበረኝ፡፡ ጦርነቱ በተጀመረበት በዚያ ሰዓት ግን ምንም አላቅማማሁም፡፡ አሁን ሌላ ነገር መስራቱን ጨርሶም አላስበውም፡፡”

ያራና ኮርኖኹዝ የተዋጊው ጦር ህክምና ቡድንን በመቀላቀል የዩክሬንን ጦር ማገልገል ከጀመረች ሁለት ዓመት ሆናት፡፡ ሠራዊቱን ስለመቀላቀሏ እንዲህ ትላለች፦

“ ሠራዊቱን የተቀላቀልኩት ሁልጊዜም እሱን ማድረግ እፈልግ ስለነበር ነው፡፡ የገባሁት ግን እኤአ በ2014 አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ያን ጊዜ ሚያዝያ ወር ውስጥ ልጅ ወልጄ ነበር፡፡ እኤአ በጥር 2020 ሠራዊት ውስጥ የነበረው የፍቅር ጓደኛዬ ግንባር ላይ የሞተበት ወቅት ነበር፡፡ ከዚያ በቃ እሱን ለማስታወስ ስል ጦሩን ለመቀላቀል ወሰንኩ፡፡”

በዩክሬን ጦር ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ጋር እኩል እየተፋለሙ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:03:48 0:00

እንደ ዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ገለጻ ከሆነ እኤአ በ2021 መጨረሻ አካባቢ ወደ 32ሺ የሚጠጉ ሴቶች የዩክሬንን ተዋጊ ጦር ተቀላቅለዋል፡፡

ካተሪያና ፕራይማክ የዩክሬን ሴት አርበኞች ንቅናቄ ተባባሪ መስራች ናት፡፡

ላለፉት ሰባት ዓመታት በዩክሬን ጦር ውስጥ ስለሴቶች መብት ስትታገል ቆይታለች፡፡

ይህም ሁሉ ጥረት ተደርጎ ግን አሁንም ሴቶች እና ወንዶች በሠራዊቱ ውስጥ እኩል አይታዩም ትላለች፡፡

ይህንንም ስትገልጸው፦

“ሴት ልጅ ሠራዊቱን ከተቀላቀለች፣ ቤት ውስጥ ልጅ ኖሯት ከባሏም ከቤት የሚጠበቋት ከሆነ ስለዚያች ሴት ወግ አጥባቂው ማህበረሰብ ምን ሊል እንደሚችል ልታስቢ ትችያለሽ፡፡ ምንም እንኳ ሴት ልጅ የፈለገችውን የሥራ መስክ የመምረጥ መብት ቢኖራት ወይም ባልና ሚስት ውትድርና ውስጥ ሊገቡ ቢችሉ ማለት ነው፡፡” ብላለች፡፡

“በዚያ ላይ ደግሞ ሴቶች የወንድ ባልደረቦቻቸውን አክብሮት ለማግኘት እጥፍ ድርብ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡” የምትለዋ ኤቭጌንያ ኤርማልድ ይህን አክላበታለች ፦

“እዚህ ላይ ግልጽ መሆን እፈልጋለሁ፡፡ ከሁሉም የከፉት ሁለቱ ሳምንታት ከባድ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ጠንክራ ሠራተኝነቴንና ጽናቴን አረጋጫለሁ፡፡ ወንዶችም ሙሉ ለሙሉ ተቀብለውኛል፡፡ አሁን ግን ታውቂያለሽ?! በቃ ለኔ እንደ ቤተሰቤ ናቸው፡፡”

እኤአ በ2014 የመጀመሪያው ወታደራዊ ርምጃ ዶናባስ ግዛት ላይ ከተወሰደበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት 8 ዓመታት በርካታ ሴቶች በሠራዊቱ ውስጥ ከፍ ያለውን ሥፍራ እያገኙ መጥተዋል፡፡

የዩክሬን ሴት አርበኞች ንቅናቄም ቢሆን በሠራዊቱ ውስጥ ደህንነትና መከላከልን ማዕከል ባደረገው አገልግሎት ውስጥ እያስመዘገቡ የመጡት የጾታ እኩልነት ለውጥ ቀላል እሚባል አይደለም፡፡

ካተሪያና እንዲህ ትገልጸዋለች ፦

“ ሴቶች አሁን በእኩልነት እየታዩ ነው፡፡ መብት እንዳላቸው ፍጥሮች እየተወሰዱ ነው፡፡ ያ ትልቅ እምርጃ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሰራዊቱ ውስጥ ማንም ሰው ስለ ወሲባዊ ጥቃትም ሆነ ማስፈራራት የሚያናገር አልነበረም፡፡ አሁን ግን ይህ ጉዳይ አይነኬ መሆኑን ቀርቷል፡፡ እየሰራንበት ነው፡፡

“ለአሁኑ ግን” ትላለች ካተሪያና “ለአሁኑ ግን ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች እጅግ በጣም አንገብጋቢ የሆነው ጉዳይ ለሁለቱም መሣሪያና መድሃኒት ማግኘት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከዩክሬን ጋር የተሰለፉ ምዕራባውያን አጋር አገሮች በሚችሉት ሁሉ መርዳት ይኖርባቸዋል” ብላለች፡፡

XS
SM
MD
LG