በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ አል-ሸባብን ከአየር ድብድባ 27 አባላቱን ገደለች


በሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት ጥያቄ መሠረት የሃገሪቱን ብሔራዊ ጦር ያጠቁ የነበሩ የአል-ሸባብ አሸባሪዎችን ከአየር መደብደቡን የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ አስታወቀ።

“ዕዙ ባከናወነው የቅድሚያ ግምገማ መሠረት በጥቃቱ 27 የአል-ሸባብ አሸባሪዎች ሲገደሉ፣ በጥቃቱ የተጎዳ ምንም ሲቪል የለም” ብሏል የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ ዛሬ ባወጣው መግለጫ።

የአሜሪካ ኃይሎች አጋሮችን ለመከላከል የአየር ጥቃት ለማድረግ ፈቃድ አላቸው ብሏል መግለጫው።

መግለጫው በመቀጠል፣ “የአየር ጥቃቱ የሶማሊያ ብሔራዊ ሰራዊትና የአፍሪካ ህብረት ሃይሎች በሂራን ክልል በሚገኘው አል-ሸባብ ላይ የሚያደርጉትን ዘመቻ እንዲቀጥሉና አል-ሸባብን እንዲበታትኑ አስችሏቸዋል” ሲል መግለጫው አክሏል።

ዘመቻውም በሶማሊያ ጦርና በአፍሪካ ህብረት ሃይሎች ቅንጅት ከአምስት ዓመት ወዲህ የተደረገ ትልቁ ዘመቻ ነው ብሏል።

ሲቪሎች እንዳይጎዱ ትልቅ ጥንቃቄ እንደሚደረግና፣ ይህ ጥረትም በሲቪሎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ከሚያደርሰው አል-ሸባብ በተቃራኒ የቆመ ነው ሲል የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ዕዝ በመግለጫው አስታውቋል።

እንደ አልሸባብ ያሉ አክራሪና አጥፊ ድርጅቶች በሶማሊያ፣ በቀጠናውና በአሜሪካ ጥቅሞች ላይ አደጋ የጋረጡ ናቸው ያለው ዕዙ፣ የሶማሊያን ሰላምና መረጋጋት እያወከ ያለውን አልሸባብ ለመደምሰስ በሚያደርጉት ጥረት አሜሪካ የሶማሊያንና የአፍሪካ ኅብረት የተቀናጀ ትብብር ትደግፋለች ሲል መግለጫውን ደምድሟል።

XS
SM
MD
LG