በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለሁለት የኮቪድ የማጠናከሪያ ክትባቶች ፈቃድ ሊሰጥ ነው


የዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር /ኤፍዲኤ/
የዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር /ኤፍዲኤ/

የዩናይትድ ስቴትስ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር /ኤፍዲኤ/ አሜሪካውያን በፊት ከወሰዱት የኮቪድ-19 ክትባት የተለየ ማጠናከሪያ ክትባት መከተብ እንዲችሉ ሊፈቅድ መሆኑ ተጠቆመ።

የፌዴራሉ መንግሥት የመድሃኒት ተቆጣጣሪ መሥራያ ቤት ለሞደርና እና ለጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮቪድ ክትባቶች የማጠናከሪያ ክትባት ነገ ረቡዕ በይፋ ፈቃድ ይሰጣል። በዚያው መግለጫ ላይ የተለያዩ ክትባቶች በማጠናከሪያነት እንዲሰጡ ይፈቅዳል ተብሎ ይጠበቃል።

በፋይዘር የተሰራው እና በሁለት ጊዜ የሚሰጠውን ክትባት ማጠናከሪያ የተወሰኑ ሰዎች የመጀመሪያቸውን ካጠናቀቁ ከስድስት ወር በኋላ እንዲከተቡት የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል ፈቃድ መሰጠቱ ይታወሳል። ዕድሜያቸው ከስድሳ አምስት ዓመት በላይ ለሆኑ፣ በአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ለሚኖሩ እንዲሁም መምህራን እና የጤና ሰራተኞች ለመሳሰሉ የሥራ ሁኔታቸው ለቫይረሱ ሊያጋልጣቸው የሚችሉ ሰዎችንና የቀደሙ የጤና ችግሮች ያሏቸው ሰዎችን ይጨምራል።

ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነ በብሄራዊ የጤና ተቋም /ኤንአይኤች/ የተካሄደ አንድ ጥናት ባለነጠላ መርፌውን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰኑን ክትባት የተከተቡ ሰዎች የሞደርናው ማጠናከሪያ ክትባት ሲሰጣቸው የተፈጥሮ መከላከያቸው በሰባ ስድስት እጥፍ ሲጨምር በንፅጽር፤ የፋይዘሩን ማጠናከሪያ የወሰዱት ደግሞ የተፈጥሮ መከላከያቸው ያደገው በሰላሳ አምስት ዕጥፍ እንደሆነ አመልክቷል።

ሁለተኛ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት የተወጉት ደግሞ የተፈጥሮ መከላከያቸው የጨመረላቸው በአራት ዕጥፍ ብቻ መሆኑን ጥናቱ ጠቁሟል። ለሞደርና እና ለጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች ማጠናከሪያ ክትባት እንዲፈቀድ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው ይህን የጥናት ውጤት ተከትሎ መሆኑ ተመልክቷል።

በሌላ ዜናም የዩናይትድ ስቴትሷ ዋሽንግተን ክፍለ ሀገር የፉትቦል አሰልጣኝ ለክፈለ ሀገሩ ሰራተኞች በሙሉ የኮቪድ-19 ክትባት መከተብን ግዴታ የሚያደርገውን መመሪያ ለማክበር ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከስራ መባረራቸው ተገለጠ።

ክትባቱን የማይከተቡት በሃይማኖታቸው ምክንያት መሆኑን የተናገሩት የአርባ ሁለት ዓመቱ ሮሎቪች በዓመት 3.2ሚሊዮን ዶላር ደመወዝ ከሚያገኙበት ሥራቸው የተባረሩ ሲሆን አራት ረዳት አሰልጣኞቻችውም አንከተብም በማለታቸው ተባርረዋል።

XS
SM
MD
LG