በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"የዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ-19 ይዞታ ትክክል ባልሆነ አቅጣጫ ላይ ነው" ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ


 ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ
ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ

የዩናይትድ ስቴትስ ዋናው የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ረገድ ትክክል ባልሆነ ይዞታ ላይ ነን ሲሉ ተናገሩ።

የዩናይትድ ስቴትስ የአለርጂ እና የተላላፊ በሽታዎች ተቋም ዋና ዳይሬከተሩ ዶ/ር ፋውቺ ትናንት ዕሁድ በሲኤንኤን “ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” ዝግጅት ላይ ቀርበው በሰጡት ቃል ከጠቅላላው ህዝብ ሃምሳ ከመቶው አልተከተበም፣ ያ አስቸጋሪ ነገር ነው" ብለዋል።

ዶ/ር ፋውቺ ይህን ያሉት እምቢ አንከተብም የሚሉ ነዋሪዎች ባሉባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች የቫይረሱ ተያዦች ቁጥር እየጨመረ ባለበት በአሁኑ ወቅት ሲሆን የቫይረሱ ስርጭት እየተባባሰ የመጣው ዴልታ በተባለው የቫይረሱ ዝርያ ሳቢያ መሆኑ እያተነገረ ነው።

የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከፍተኛ የጤና ጉዳዮች አማካሪው ዶ/ር ፋውቺ ራሳችንን አደጋ ላይ እየጣልን ነው ብለዋል። ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ዴልታውንም ዝርያ ጭምር በከፍተኛ ደረጃ ይከላከልላቸዋል ብለዋል። ይሁን እንጂ የክትባት መርሃ ግብሩ ፍጥነት ከሚያዝያ መጀመሪያ ወዲህ ከሰማኒያ በመቶ በሚበልጥ መጠን እንደቀነሰ ተገልጿል። ሎስ አንጀለስን እና ሴንት ሉዊስን ጨምሮ አንዳንድ የአሜሪካ ከተሞች ነዋሪዎች የተከተቡም ይሁኑ፣ አይሁኑ ደጅ ካልሆኑ በስተቀር ዝግ ስፍራዎች የአፍና አፍንጫ ጭንብል እንዲያደርጉ አዳዲስ ትዕዛዞችን አውጥተዋል። ሌሎችም ከተሞች ተመሳሳይ መመሪያ ለማውጣት እያቀዱ ናቸው።

በዩናይትድ ስቴትስ ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ-19 መረጃ አጠናቃሪ ማዕከል መሰረት በዓለም ዙሪያ የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች ቁጥር ከአንድ መቶ ዘጠና ሚሊዮን አልፏል። ቫይረሱ በሚያስከትለው በኮቪድ-19 ምክንያት ለህልፈት እንደተዳረጉ የተረጋገጠው ሰዎች ቁጥር ደግሞ አራት ሚሊዮን አንድ መቶ ሃምሳ ዘጠኝ ሽህ አንድ መቶ ስምንት ገብቷል።

XS
SM
MD
LG