ዩናይትድ ስቴትስ ኮቪድ-19ን በተመለከተ በትክክለኛ አቅጣጫ በመራመድ ላይ ነች ሲሉ ዶ/ር አንተኒ ፋውቺ ተናገሩ።
በሚሊዮኖች የተቆጠሩ አሜሪካውያን ክትባቱን እየወሰዱ በመሆናቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሆኖም በበሽታው የሚጠቃው ሰው ቁጥር ባለበት ከፍ ያለ መጠን መቀጠሉ አሳሳቢ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም።
ፋውቺ በኤንቢሲ ቴሌቨዥን ቀርበው በሰጡት ቃል የኮሮናቫይረስ ሥርጭት ይዞታ በቀን ስድሳ ሺህ ሰው የሚያዝበት ሁኔታ ላይ መረጋጋቱ ወረርሽኙ በከፍተኛ መጠን ሊያሻቅብ እንደሚችል የሚያመለክት መሆኑን ገልጸዋል።
ጣሊያንን በምሳሌነት የጠቀሱት የዩናይትድ ስቴትሱ ከፍተኛው የተላላፊ በሽታዎች አዋቂው ፋውቺ በጣሊያን በቫይረሱ የሚያዘው ሰው ቁጥር በተረጋጋበት ጊዜ ለመከላከያ ተወስደው የነበሩ ርምጃዎች መነሳታቸውን አስታውሰው ያ ሲሆን አሁን እየታየ ያለውን የተጠቂዎች ቁጥር መጨመር በማስከተሉ ባለሥልጣናቱ አንዳንዶቹ የሃገሪቱ አካባቢዎች ላይ የእንቅስቃሴ መዝጋት ርምጃ እንዲወስዱ አስገድዷል ብለዋል።
አሜሪካውያን የቫይረሱን መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ማደረጉን እንዲቀጥል በተለይ ደግሞ በማስክ መሸፈኑን እንዲቀጥል ፋውቺ አጥብቀው መክረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም ዙሪያ ካሉት ወደአንድ መቶ ሃያ ሚሊዮን የተጠጉ የቫይረሱ ተጋላጮች ውስጥ ከፍተኛው የሆነው ሃያ ዘጠኝ ነጥብ አራት ሚሊዮኑን ይዛለች። ብራዚል አስራ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን፣ ህንድ አስራ አንድ ሚሊዮን ይዘው ዩናይትድ ስቴትስን ይከተላሉ።