በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፌስቡክ የኢትዮጵያ ምርጫ እየተቃረበ ባለበት "ሃሰተኛ" ያላቸውን ገፆችን መዝጋቱን አስታወቀ


ፌስቡክ ኢትዮጵያ ውስጥ የፊታችን ሰኞ ሊካሄድ በታቀደው ስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ዋዜማ “የአገር ውስጥ ተጠቃሚዎችን ዒላማ ያደረገ እና ከኢትዮጵያ የመረጃ ደኅንነት ኤጄንሲ /ኢንሳ/ ጋር ግንኙነት ካላቸው ግለሰቦች ጋር የተገናኘ ነው” ያለውን “ሃሰተኛ” ያለውን የማኀበራዊ ገፆች መረብ መዝጋቱን ማስታወቁን ሮይተርስ ዘገበ።

“መረቡ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ፓርቲያቸውን ብልፅግናን ጨምሮ በዋናነት በአማርኛ የተዘጋጁ ዜናዎችና ዘገባዎችን ሲያወጣ ነበር” ብሏል። “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር /ኦነግ/ን፥ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲንና የትግራይ ነፃ አውጭ ግንባርን ጨምሮ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ድርጅቶችን የሚነቅፉ አስተያየቶችንም ያወጣ እንደነበር” መናገሩን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ኢንሳ ዋና ዳይሬክተር በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ጠይቆ ምላሽ እንዳላገኘ ሮተርስ ጠቅሷል።

“ፌስቡክ ስለወሰደው እርምጃ ምላሽ የተጠየቁት የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሬስ ተጠሪ ቢል ለኔ ስዩም "ኢንሳ በሰላም ሚኒስቴር ሥር የሚተዳደርና ነፃ ተቋም ስለሆነ ጥያቄችሁን እዚያ አቅርቡ" ማለታቸውን የዜና አውታሩ ገልጿል።

የፊታችን ሰኞ በሚከናወነው ምርጫ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ከያዙ ወዲህ ለምርጫ የሚቀርቡት ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

ከሀገሪቱ የምርጫ ክልሎች መካከል በተለያዩ ጸጥታ ነክ፥ የሎጅስቲክ እና ልዩ ልዩ ምክንያቶች ሃምሳ ዘጠኙ በሚሆኑት ላይ ምርጫው የፊታችን ሰኛ ሳይሆን ጳጉሜ አንድ ቀን እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። በትግራይ ክልልም ከግጭቱ ጋር በተያያዙ የተለያዩ ምክንያቶች ምርጫው እንደማይካሄድ ይታወቃል። የሆነ ሆኖ ፌስቡክ የዘጋቸው አካውንቶች እንቅስቃሴያቸው በቀጥታ ትግራይ ክልል ውስጥ ባለው ግጭት ላይ ያተኮረ እንዳልነበረ ገልጿል።

ፊስቡክ አያይዞ አንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ባለአካውንቶች ከመረቡ ገጾች አንዱን ወይም ከአንድ በላይ ይከተሉዋቸው እንደነበርና ወደ 766፣000 አካውንቶች ከቡድኖቹ አንዱን ወይም ከዚያ በላይ መቀላቀላቸውን አመልክቷል።

“በፌስቡክ እና በኢንስታግራም ላይ ተከፍተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት አካውንቶች የወልና የግል ገፆች በተቀናጀ መንገድ ሃሰተኛ እንቅስቃሴ ማድረግን የሚከለክለውን ደንባችንን ጥሰው አግኝቻቸዋለሁ” ብሏል።

ፌስቡክ ካለፈው የአውሮፓ 2020 ጀምሮ በቀጠሉት የ2021 ወራት የመረቡ እንቅስቃሴ እየጨመረ መምጣቱን እንዳስተዋለ ገልፆ በቅርቡም ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ ላይ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች የተመለከተ ትችት አውጥቶ እንደነበር ጠቁሟል።

መረቡ በተለያዩ መድረኮች ላይ ማስታወቂያ ለማውጣት በአሜሪካ ዶላር በተፈፀመ ክፍያ 6,200 ዶላር እንዳወጣ ፌስቡክ መናገሩን ሮይተርስ ያጠናቀረው ዘገባ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG