በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሪፐብሊካን የተወካዮች ም/ቤትን ዴሞክራቶች ሴኔቱን ተቆጣጠሩ


አዲስ የተመረጡ የኮንግረስ አባላት
አዲስ የተመረጡ የኮንግረስ አባላት

በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገው የፕሬዚዳንታዊው ዘመን የአጋማሽ ጊዜ የምክር ቤት አባላት ምርጫ የሪፐብሊካን ፓርቲ አብዛኛውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፉ ተገልጿል፡፡

ሳምንት ከፈጀ የድምጽ ቆጠራ በኋላ ዛሬ ይፋ በተደረገው ውጤት መሰረት የሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት አብላጫውን የህዝብ ተወካዮች መቀመጫ ሲያሸንፉ የዴሞክራቲክ ፓርቲ አባላት ደግሞ የህግ መወሰኛውን ምክር ቤት(ሴኔቱን) መቆጣጠራቸው ተመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ በመጭው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ የምክር ቤቱን መቀመጫዎች የሚቆጣጠሩት ፓርቲዎች ሁለቱም በጠባብ ልዩነት ያሸነፉ በመሆናቸው አጀንዳዎቻቸውንና ፖሊሲዎቻቸውን በፈለጉት መንገድ ለማስፈጸም ያላቸው እድል የተጣበበ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደንም የተከፋፈሉ ይሆናሉ በተባሉ ምክር ቤቶች ውስጥ ዋና ዋና አጀንዳዎቻቸውን ለማስፈጸም ብርቱ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ከወዲሁ እየተነገረ ነው፡፡

ሪፐብሊካን የህግ መወሰኛው ምክር ቤት አባላት ሴንተር ሚች መካኔልን በምክር ቤቱ የፓርቲው መሪ ሆነው ባሉበት እንዲቆዩ በድጋሚ መርጠዋቸዋል፡፡

የተወካዮች ምክር ቤት አባላትም እንዲሁ አሁን በምክር ቤቱ የሪፐብሊን ፓርቲ መሪ የሆኑትን ኬቪን መካርቲን አዲሱ አፈጉባኤያቸው አድርገው ትናንት ረቡዕ መርጠዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቀኝ አክራሪ የሆኑት በርካታ የፓርቲው አባላት ለመካርቲ ድጋፋቸውን አልሰጧቸውም፡፡

በዚህ የተነሳም መካርቲ በአፈጉባኤነት ዘመናቸው የሙሉውን ምክር ቤት ድምጽ ለማባሰባሰብ ብርቱ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሏል፡፡

የዴሞክራትም ሆነ የሪፐብሊካን ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ያላቸው ጠባብ የመቀመጫ ልዩነት ከፓርቲያቸው እንዲነጠሉ የማያበረታታና የማያዋጣ በመሆኑ ከፓርቲዎቻ አቋም ጋር ጸንተው እንዲቆሙ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

ይህ በመሆኑም የተለያየ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች አዲስ ነገር ሊጠበቅ ስለማይችል ከ2023ቱ አዲሱ ምክር ቤት ብዙም የሚጠበቅ ነገር አለመኖሩ የአሜሪካ ድምጽ ያነጋገራቸው ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

XS
SM
MD
LG