በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ ከአይኤምኤፍ ኹለት ቢሊዮን ዶላር ብድር ትሻለች


አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መሠረት፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት/አይኤምኤፍ/፣ ኹለት ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት በመወያየት ላይ እንደኾነች፣ ሮይተርስ የተቋሙን ምንጮች ጠቅሶ ዘግቧል።

ከውይይቱ ምስጢራዊነት የተነሣ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አራት የሮይተርስ ምንጮች፣ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የተቋሙ ሓላፊዎች እያደረጉ በሚገኙት ውይይት፣ አይኤምኤፍ የኢትዮጵያን የመበደር ዐቅም እየገመገመ መኾኑን ተናግረዋል።

በተቋሙ ግምገማ፣ እአአ እስከ 2026 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ ቢያንስ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ያህል የገንዘብ እጥረት ሊገጥማት እንደሚችል፣ ለውይይቱ ቅርበት ያላቸው ኹለት ምንጮች ለሮይተርስ ገልጸዋል፡፡ አሁን በግምገማ ላይ ያለው የብድር ጥያቄ ቢሳካላት እንኳ፣ ኢትዮጵያ አራት ቢሊዮን ዶላር እጥረት ሊያጋጥማት እንደሚችል፣ ቅድመ ትንበያ ተቀምጧል።

በዋሽንግተን ዲሲ እየተካሔደ ባለው የአይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ስብሰባ ላይ፣ የብድሩ ጉዳይ ውይይት እየተደረገበት ነው። “የርዳታው መጠን እስከ አሁን በቃል አልተገለጸም፤ ነገር ግን፣ ኹለቱ የገንዘብ ተቋማት፣ የአገሪቱን የመበደር ዐቅም እያጠኑ ነው፤” ሲሉ አንድ ምንጭ መግለጻቸውን የሮይተርስ ሪፖርት አክሎ አመልክቷል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ እና አስተያየት ለማግኘት፣ ሮይተርስ፥ ከአይኤምኤፍ ቃል አቀባይ፣ ከኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ እና ከብሔራዊ ባንክ ገዢው ማሞ ምሕረቱ ዘንድ ያደረገው ሙከራ እንዳልተሳካለት ገልጿል፡፡

ከኹለት ዓመት በፊት፣ ኢትዮጵያ የዕዳ መክፈያ ሽግሽግ እንዲደረግላት፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገሮች በታሰበው መሠረት አመልክታ ነበር። ኾኖም፣ ጥያቄዋ የሚስተናገድባት ሒደት፣ ለኹለት ዓመት በተደረገውና ሚሊዮኖችን ገድሎ፣ ሌሎች ብዙ ሚሊዮኖች በአፈናቀለው ጦርነት ምክንያት ተስተጓጉሏል፤ ሲል፣ ሮይተርስ ዘገባውን አጠቃሏል።

XS
SM
MD
LG