በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጄከብ ዙማ የእስር ቅጣት ተፈረደባቸው


ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጄከብ ዙማ
ፎቶ ፋይል፦ የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጄከብ ዙማ

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጄከብ ዙማ የአንድ ዓመት ከሦስት ወር እስራት ቅጣት ተፈረደባቸው። የደቡብ አፍሪካ ከፍተኛው ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ላይ ዛሬ የእስራት ቅጣቱን የወሰነባቸው በሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ፈጽመዋል የተባሉትን በርካታ የሙስና ወንጀሎች በሚመረምረው ችሎት ፊት ባለመቅረብ ፍርድ ቤት በመዳፈር ጥፋት ፈጽመዋል ብሎ ነው።ዙማ በቀጣዮቹ አምስት ቀናት ውስጥ ለፖሊስ እጃቸውን እንዲሰጡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የሰባ ዘጠኝ ዓመቱ ጄከብ ዙማ ለዘጠኝ ዓመታት ሥልጣን ላይ በቆይበት ዘመን ከመንግሥታዊ የንግድ ተቋማት እና ሚኒስቴሮች ገንዘብና ንብረት ዘርፈዋል ተብለው ብዛት ያላቸው ክሶች የቀረቡባቸው ሲሆን ጉዳዩን የሚመረምረው ልዩ ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ታዘው ነበር።

አንዳችም ወንጀል አልፈጸምኩም ብለው አጥብቀው ሲከራከሩ እና በምርመራ አልተባበርም ብለው የቆዩት ዙማ ምርመራውን የሚመሩትን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ ዳኛ ሬይመንድ ዞንዶን የቆየ ቂም የያዙብን ሰው ናቸው ብለው ወንጅለዋል።

ዙማ ሃገራቸው ከአውሮፓ የጦር መሳሪያ ኩባኒያዎች የጦር አውሮፕላኖች እና የባህር ሃይል መርከቦች ግዢ ስታከናውን የማጭበርበር፥ ገንዘብ በተዘዋዋሪ ማሸጋገር እና ሌላም የሙስና ተግባር ፈጽመዋል ተብለው ተከሰዋል።

በዙማ ላይ የተከፈተው ክስም የአሁኑ ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ መንግሥቱን እና ገዢውን ፓርቲ የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ ውስጥ ለመመንጠር የያዙት ዕቅድ አካል መሆኑ ተገልጿል።

XS
SM
MD
LG