በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቱኒዚያ ፓርላማ ወደሥራው እንዲመለስ የአውሮፓ ህብረት አሳሰበ


የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ
የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ

የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ ፓርላማውን ማገዳቸውን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማባረራቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ህብረት ባወጣው መግለጫ፣ የሀገሪቱ ዲሞክራሲ እና መረጋጋት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አጽንዖት ሰጥቶ አሳስቧል።

የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ዛሬ ማክሰኞ ባወጡት መግለጫ በቱኒዚያ "በተቻለ ፍጥነት ተቋማዊ መረጋጋት እንዲመለስ ማድረግ ያስፈልጋል፤ በተለይም የፓርላማው የሥራ እንቅስቃሴ፥ የመሰረታዊ መብቶች መከበር እንዲመለስ ያስፈልጋል። ምንም ዓይነት የሁከት አድራጎት ሊፈጸምም አይገባም" ሲሉ ተማጽነዋል።

የቱኒዚያ ፕሬዚደንት ካይስ ሳኢድን በስልክ እንዳነጋገሯቸው የገለጹት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን በበኩላቸው ለቱኒዚያ ዲሞክራሲ ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

"ፕሬዚደንት ሳኢድ በቱኒዚያ የአስተዳደር መሰረት የሆኑትን የዲሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብት መርሆችን አጥብቀው እንዲከተሉ እና ከሁሉም የቱኒዚያ የፖለቲካ ተዋናዮች እና ከህዝቡ ጋር ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቤላቸዋለሁ" ብለዋል።

የቱኒዚያ ፕሬዚዳንት ዕሁድ ዕለት ለወሰዱት እርምጃ ምክንያታቸው ሃገሪቱ ያለችበት የከበደ የኢኮኖሚ ችግር እና ፖለቲካዊ ውጥረቱ መሆኑን ገልጸው እርምጃውን እንዲወስድ ህገ መንግሥቱ ይፈቅድልኛል ብለዋል። በሃገሪቱ ፓርላማ አብላጫ መቀመጫ ያለው ኢናዳ ፓርቲ መሪና የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ራቼድ ጋኑቺ በበኩላቸው የፕሬዚዳንቱ እርምጃ ከመፍንቅለ መንግሥት የሚቆጠር ነው በማለት ኮንነዋል፤ ፓርላማው ሥራውን እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

ሌሎች ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎችም መፈንቅለ መንግሥት ነው ያሉ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ ክሱን ውድቅ አድርገዋል።

XS
SM
MD
LG