በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከኒዠር ሊያስወጡ ነው


በኒዤር ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንቱን አስወግዶ ሥልጣን የተቆጣጠረው ጁንታ ተቃዋሞዎች የፈረንሳይ ኤምባሲ ደጃፍ ተሰብስበው፤ ኒያሜ፣ ኒዥር
በኒዤር ባለፈው ሳምንት ፕሬዝደንቱን አስወግዶ ሥልጣን የተቆጣጠረው ጁንታ ተቃዋሞዎች የፈረንሳይ ኤምባሲ ደጃፍ ተሰብስበው፤ ኒያሜ፣ ኒዥር

በኒዠር ወታደራዊው ቡድን ስልጣን ከተቆጣጠረ ከአንድ ሳምንት በኃላ፣ ፈረንሳይ ዜጎቿን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ዜጎችን የማስወጣት ጥረት እንደምትጀምር ዛሬ ማክሰኞ አስታውቃለች።

የፈረንሳይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ዜጎችን የማስወጣት ውሳኔ የተደረሰው፣ ከትላንት በስቲያ እሁድ በኒያሜ ከሚገኘው የፈረንሳይ ኤምባሲ ደጃፍ በርካታ ህዝብ ተሰብስቦ ጥቃት ከደረሰ እና ፈረንሳይ ወታደራዊ ጣልቃ ለመግባት እያሴረች ነው በሚል ኒዠር ውንጀላ ከሰነዘረች በኃላ ነው። የኒዠር አየር ክልል በመዘጋቱም የፈረንሳይ ዜጎች በራሳቸው ከሀገር መውጣት አለመቻላቸውንም የሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።

ዜጎችን በአየር ለማስወጣት ዝግጅት ላይ መሆኑን ያመለከተው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ፣ ዜጎችን የማስወጣቱ ስራ ዛሬ እንደሚጀምር እና በጣም ውስን በሆነ ግዜ ውስጥ እንደሚከናወን ይፋ አድርጓል።

ለሃገር ጉብኝት የተጓዙትን እና በኒዠር ነዋሪ የሆኑ ባሁኑ ወቅት ግን ከኒዠር ውጪ የሚገኙ ፈረንሳውያንን ሳይጨምር፣ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው 600 የሚደርስ የፈረንሳይ ዜጎች በዚያች አገር እንዳሉ ተገምቷል።

በተመሳሳይ፣ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዩ ታጃኒ፣ ጣሊያን ዜጎቿን ከኒያሜ ለማስወጣት ልዩ በረራ ማዘጋጀቷን በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አመልክተዋል። በዋና ከተማይቱ ኒያሜ ብቻ 90 የጣሊያን ዜጎች እንደሚገኙ እና በመላው ኒዠር ደግሞ ቁጥራቸው 500 የሚደርስ የጣሊያ ዜጎች እንደሚኖሩ ተገልጿል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስ) በመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ላይ ማዕቀብ የጣለ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንት መሀመድ ባዙም ወደ ስልጣን ካልተመለሱ ጠንካራ የኃይል እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል አስጠንቅቋል። ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፖ ህብረትም የባዙም መንግስት በአስቸኳይ ወደ ስልጣን እንዲመለስ ጠይቀዋል።

በወታደራዊ መንግስት የሚመሩት ሁለቱ የኒዠር ጎረቤት ሀገራት፣ ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ ሰኞ እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በኒዠር ላይ የሚወሰድ ማንኛውም ወታደራዊ እርምጃ "በቡርኪና ፋሶ እና በማሊ ላይ እንደታወጀ ጦርነት ይቆጠራል" ያሉ ሲሆን፣ ሌላኛዋ በወታደር የምትመራው ጎረቤት ሀገር ጊኒም እንዲሁ፣ ኤኮዋስ በኒዠር ላይ በተጣለው ማዕቀብ እና ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ዙሪያ ተቃውሞ አሰምታለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG