በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ መሪዎች በፀጥታ ቀውስ ዙሪያ ውይይት አካሄዱ


የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ በሚገኘው በኤሊዜ ቤተመንግሥት ለሚካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የሚገኙ የአውሮፓ መሪዎችን መምጣት እየተጠባበቁ፤ ፓሪስ
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ በሚገኘው በኤሊዜ ቤተመንግሥት ለሚካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ የሚገኙ የአውሮፓ መሪዎችን መምጣት እየተጠባበቁ፤ ፓሪስ

ዩናይትድ ስቴትስ በተከታታይ እየወሰደቻቸው ያለቻቸው ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃ ገብነቶች ከአውሮፓ ሀገራት ጋራ ባላት ትብብሮች ዙሪያ ጥርጣሬ በመፍጠራቸው፣ የአውሮፓ መሪዎች ትላንት ሰኞ ፓሪስ ላይ በፀጥታ ቀውስ ዙሪያ ስብሰባ አካሂደዋል።

በኤሊዜ ቤተመንግሥት በተካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ላይ ከተገኙት የአውሮፓ መሪዎች መካከል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር፣ የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል-ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ዋና ጸሃፊ ማርክ ሩታ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን እና ሌሎች አመራሮች ይገኙበታል።

ከስብሰባው በኋላ ለጋዜጠኞች ንግግር ያደረጉት የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመር "ጥያቄ ውስጥ የገባው የዩክሬን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብቻ አይደለም። ለአውሮፓም የህልውና ጥያቄ ነው። ስለዚህ ለእንግሊዝ ብሔራዊ ጥቅም ወሳኝ ነው" ብለዋል።

"ዩናይትድ ስቴትስ ኔቶን ጥላ እንደማትወጣ ግልፅ ነው" ያሉት ስታርመር "እኛ አውሮፓውያን ግን የበለጠ ማድረግ ይጠበቅብናል። ኃላፊነትን የመጋራት ጥያቄ አዲስ ባይሆንም፣ አሁን ግን አንገብጋቢ ሆኗል። አውሮፓውያን በወጪም ኾነ ባለን አቅም የበለጠ ማድረግ አለብን" ብለዋል።

ዘላቂ የሰላም ስምምነት ካለ፣ እንግሊዝ ከሌሎች ጋራ በመሆን ጦሯን ለማስፈር ዝግጁ መሆኗን ያመለከቱት ስታርመር፣ ከጀርባ ግን ዩናይትድ ስቴትስ መኖር አለባት ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። "ምክንያቱም ሩሲያ ዩክሬንን በድጋሚ እንደማታጠቃ የመከላከያ ብቸኛ ዋስትናው የዩናይትድ ስቴትስ የጸጥታ ዋስትና ነው" ሲሉም አብራርተዋል።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ምርጫ የሚጠብቃቸው የጀርመኑ ሾልዝ በበኩላቸው፣ አውሮፓ እና ዩክሬን የሰላም ንግግሩ አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG