ዋሽንግተን ለዩክሬን የምትሰጠው የጦር መሣሪያ ዕርዳታ በድንገት እንዲቋረጥ በተደረገበት፤ ሃሳብ የገባቸው የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች ከሩስያ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ጋር በተዛመደ የሕብረቱን የመከላከያ አቅም ለማጎልበት በሚያስችሉ መንገዶች ዙሪያ ለመምከር የፊታችን ሃሙስ ብረስልስ ላይ እንደሚሰበሰቡ ተገለጠ።
“ጥያቄው የአውሮፓ ደኅንነት በተጨባጭ አደጋ ላይ ወድቋል፣ ወይም አውሮፓ ደህንነቷን ለማስከበር የምትወስደውን ኃላፊነት ማሳደግ አለባት’ የሚለው አይደለም” ያሉት የአውሮፓ ኮሚሽነር ኡርሱላ ቮን ደር ሊን “ከፊታችን ያለው ትክክለኛ ጥያቄ አውሮፓ ሁኔታው በሚጠይቀው ደረጃ ቁርጠኛ ምላሽ ለመስጠት፣ ብሎም በሚፈለገው ፍጥነት እና እቅድ ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የሕብረቱ ኮሚሽነር ከጉባኤው አስቀድሞ በሰጡት አስተያየት፣ በርካታ ዝርዝሮች ያቀፈውን የ840 ቢሊዮን ዶላር የመከላከያ በጀት ዕቅድ 27 አባል አገራት ላሉት ሕብረት አቅርበዋል።
ኮሚሽነሯ ያስተላፉት ይህ መልእክት ‘የዩናይትድ ስቴትስ የአጋርነት ተሳትፎ የሚጓደልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል’ በሚል ሥጋት የአሕጉሪቱ መሪዎች በተገኙባቸው በርከት ያሉ አስቸኳይ ስብሰባዎች ላይም ተስተጋብቷል። ዋሽንግተን ‘የአውሮፓ መሪዎች ተጨማሪ ኃላፊነት እንዲወስዱ’ በሚል ለዓመታት ስታሰማ የቆየችው ጥሪ እና የወቅቱ ሁኔታ አዲሱን የአውሮፓ የመከላከያ ወጪ ዕቅድ ቅርብ አድርገውታል።
ይሁንና የሕብረቱ አባላት አንዳንድ ፈተና ከገጠማቸው መንግሥታት እና ኢኮኖሚዎች፤ ሁኔታውን አስመልክቶ የጎላ ጥርጣሬ የሚያንጸባርቁ ማሕበረሰቦች እስካሉባቸው፤ እና በአመዛኙ ለሩስያ ተስማሚ የሆነ ቀኝ ዘመም አመለካከት ያላቸው ኃይሎች እየገነኑ የመጡባቸው አገራት የደቀኑት ፈተና ድረስ የአሕጉሪቱን መከላከያ የማጎልበቱን ጥረት አቀበት ያደርጉታል ተብሏል።
መድረክ / ፎረም