ስፔን፣ አየርላንድ እና ኖርዌይ በመጪው ማክሰኞ ፍልስጤምን እንደ ሃገር እውቅና እንደሚሰጧት አስታውቀዋል።
ውሳኔው ለፍልስጤማውያን የረጅም ጊዜ መሻት መልስ የሰጠና እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የከፈተችውን ጥቃት ተከትሎ በተከሰተው እልቂትና ሰብአዊ ቀውስ ዓለም ቁጣውን በሚገልጽበት ወቅት የመጣ ነው።
በሁለቱ የአውሮፓ ኅብረት ዓባል ሃገራትና በኖርዌይ ዛሬ ረቡዕ የተገለጸው ውሳኔ፣ ሌሎችንም የኅብረቱ ዓባላት እውቅና እንዲሰጡ የሚያነሳሳ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ የሚያደርግ ነው ተብሏል። ይህም የእስራኤልን መገለል ይበልጥ እንደሚያባብስ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት ከአውሮፓ ኅብረት ዓባል ሃገራት ውስጥ ሰባቱ ብቻ ለፍልስጤም እውቅና ይሰጣሉ። ማልታ እና ስሎቬንያም ተመሳሳይ ውሳኔ ሊሰጡ እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከተወከሉት 190 ሀገራት ውስጥም 140 የሚሆኑት ለፍልስጤም ሉዓላዊ ሃገር መሆን እውቅና ሰጥተዋል።
መድረክ / ፎረም