በደቡባዊ እና ማዕከላዊ አውሮፓ ከ40 ዲግሪ ሰልሲየስ በላይ የናረው ሙቀት ባለሥልጣናት ለሕዝቡ ማስጠንቀቂያ እንዲያውጁ አስገድዷል።
የደን ቃጠሎ እና በከተሞች ደግሞ የእገረኛ መጓጓዣ መንገዶች ሲቀልጡ ተስተውሏል።
ከጣልያን እስከ ሮማኒያ ሰዎች ለሽርሽር የሚወጡ ከሆነ በጥንቃቄ እንዲያሽከረክሩ፣ ውሃ በብዛት እንዲጠጡ፣ ሙቀቱ ከፍተኛ ደረጃ በሚደርስበት ሰዓት ደግሞ ከቤት እንዳይወጡ አሳስበዋል።
የጣልያን ባለሥልጣናት፣ ሮምን ጨምሮ በሰባት ከተሞች የደረጃ ቀይ ማስጠንቀቂያ አውጀዋል። የሮም ከተማ ማዘጋጃ ቤት ደግሞ ነዋሪዎች የመጠጥ ውሃ የሚያገኙባቸውን ቦታዎች የሚያመለከት መተግበሪያ አውጥቷል።
ከፍተኛው ሙቀት፣ እርጥበት ባዘለው ወበቅ እንደተባባሰ እና ይህም ቀድሞውንም የጤና እክል ላለባቸው ሰዎች አደገኛ እንደሆነ የጣሊያን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በክሮዬሺያ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሲታወጅ፣ በአልባኒያ ደግሞ ከግሪክ እና ጣሊያን በሚዋሰነው ድንበር ላይ የደን ቃጠሎ ተከስቷል።
መድረክ / ፎረም