በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አባላቱ የዩክሬንን የአውሮፓ ህብረት አባል እጩነት እንደሚደግፉ ባለሥልጣናቱ እርግጠኞች ናቸው


በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የሞቱ የዩክሬን ወታደሮች ስም የአረፈበት የዩክሬን ባንዲራዎች በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ።
በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የሞቱ የዩክሬን ወታደሮች ስም የአረፈበት የዩክሬን ባንዲራዎች በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ።

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሸል የአውሮፓ ህብረት መሪዎች ሀሙስ በሚደረገው ምርጫ ዩክሬንን በዕጩነት በመምረጥ ድምጻቸውን ይሰጣሉ ብለው እንደሚተማመኑ አስታወቁ፡፡

በብራስልስ የተሰባሰቡት የአውሮፓ ህብረት መሪዎች፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት፣ በዓለም የምግብ ደህንነት ላይ በሚያሳድረው ተጽእኖና፣ እንዲሁም በአውሮፓ ተጨማሪ የኢኮኖሚ፣ ወታደራዊና ሰብአዊ ድጋፍ ላይ እንደሚነጋገሩ ተመልክቷል፡፡

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባላፈው ሳምንት ዩክሬንና አጎራባቿ የሆነችው ትንሿ አገር ሞልዶቮ ለአውሮፓ ህብረት አባል ዕጩነት እንዲቀርቡ ሀሳብ አቅርቧል፡፡ 27 ወደሚደርሱት የህብረቱ አባል አግሮች ቡድን ለመቀላቀል የእጩነት ደረጃው የመጀመሪያው እምርጃ መሆኑን ተነግሯል፡፡ የህብረቱ አባል ለመሆን ዩክሬን ዴሞክራሲያዊ መርሆዎች ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ማሟላት ይኖርባታል፡፡ ዲፕሎማቶች መስፈርቱ የሚሟላበት ሂደት አስርት ዓመታትን ሊፈጅ እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለነስኪ ለአገራቸው ህዝብ በሚያስተላልፉት እለታዊው የምሽቱ የቪዲዮ መልዕክታቸው ትናንት ረቡዕ፣ ስለዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባል እጩነት ከ11 የህብረቱ አባል አገራት መሪዎች ጋር መነጋገራቸውን ገልጸው ዛሬ ሀሙስም ተጨማሪ የስልክ ጥሪያዎችን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ከዚያ ቀደም ብለው በሰጡት መግለጫ የአውሮፓን ህብረት ለመቀላቀል ያላቸውን ተስፋ የገለጹ ሲሆን 27ቱም አገሮች የዩክሬንን የእጩነት ደረጃ ያጸድቃሉ ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡ በሌላም በኩል ዜለንስኪ ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን ዶናባስ ግዛት ከባድ የአየርና የመድፍ ድብደባዎችን ያካሄደች መሆኑን ገልጸው ዓላማው “ቀስ በቀስ ጠቅላላውን ዶናባስ ለማውደም” ነው ብለዋል፡፡

የሩሲያውን ጥቃት ለመቋቋም የሳቸው ኃይሎች ተመጣጣኝ የጦር መሳሪያዎችን በአፋጣኝ እንዲያገኙም የዩክሬኑ መሪ ተናግረዋል፡፡ በሌላም በኩል ትልቁ የቴክኖሎጂ ድርጅት ማይሮኮሶፍት የሩሲያ የደህንነት ተቋማት የዩክሬንን አጋር አገሮች የኮምፒውተር አውታረ መረብ ለማወክ በርካታ ሙከራዎችን ማድረጋቸውን አስታውቋል፡፡

የማይክሮ ሶፍት ፕሬዚዳንት ብራድ ስሚዝ “በአሁኑ ጦርነት የሚታየው የሳይበር ጥቃት ከዩክሬንም አልፎ ያለውን የሳይበር ስፔስ ልዩ ባህርይ ያመላክታል” ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ በዋሽንግተን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አለመስጠቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ከዚህ ቀደም ከአገር ውጭ ታካሂደዋለች የተባለውን የሳይበር ስለላ ተልእኮዎችን አስመልክቶ ሞስኮ በሰጠችው መግለጫ “ከሩሲያ የውጭ ፖሊሲ መርሆዎች ጋር ይጋጫል” ስትል አስተባብላለች፡፡ ጦርነቱ ከተጀመረበት አራት ወራት ጀምሮ የዩክሬን ተቋማት በሩሲያ መንግሥት የተደገፉ ጠላፊ ቡድኖች የሳይበር ጥቃት ሲካሂዳባቸው መቆየቱን ማይክሮሶፍት አስታውቋል፡፡

ተመራማሪዎችም ባወጡት ዘገባ ከዩክሬን ውጭ በ42 አገሮች የሚገኙ 128 ተቋማት በተመሳሳይ ቡድኖች በስለላ ላይ ያተኮረ የጥቃት ኢላማ መደረጋቸው ገልጸዋል፡፡ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የሳይበር ጥቃቶች ኢላማ ያደረጉት የኔቶ አባል አገሮችን መሆኑንም ተመራማሪዎቹ በግኝታቸው አመልክተዋል፡፡

XS
SM
MD
LG