ከአውሮፓ ፓርላማና ከአውሮፓ ህብረት አባላት የተወጣጡ ተደራዳሪዎች ትናንት ሀሙስ እንደ ጉጎል፣ ሜታ፣ አማዞን እና አፕል የመሳሰሉት ግዙፎቹ የዩናይትድ ስቴትስ የቴክኖሎጂ ተቋማት በገበያው ላይ ያላቸውን የበላይነት መቀነስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ታሪካዊ ከተባለ ሥምምነት መድረሳቸው ተነገረ፡፡
በብራስልስ የተሰበሰቡት ህግ አውጭዎች በዓለም ላይ ተንሰራፍተው የኢንተርኔት ዘብና ጠባቂ በመሆን በሚያወጧቸው ህግጋት የሚጫኑትን የቴክኖሎጂ ድርጅቶች ለይቶ ለማውጣት በረጅም ጊዜ መደረግና አለመደረግ የሚገባቸውን ነገሮች ለይተው ማውጣታቸውን አስታውቀዋል፡፡
የዲጂታል ማርኬት አክት (DMA) የተሰኘው የዲጂታል ገበያዎችን ለመቆጣጠር የወጣው ህግ ደንበኞችን የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግና ተፎካካሪ ድርጅቶችም በትላልቆቹ የቴክኖሎጂ ድርጅቶች እንዳይዋጡ የሚከላከል ህግ መሆኑን ተመልክቷል፡፡
በአውሮፓ ፓርላማ ድርድሩን የመሩት የጀርመን ፓርላማ አባል አንድሪያ ሽዋብ ስምምነቱ በዓለም የቴክኖሎጂ ሥራዎች ቁጥጥር ላይ አዲስ ዘመንን የሚያመጣ ነው” ብለዋል፡፡
ዋናው ፍሬ ነገር ትላልቅ የቴክኖሎጂ ድርጅቶችን በፍርድ ቤት ከሶ ለመቅጣት የሚወስደውን የረጅም ጊዜ ሂደትና ውጣ ውረድ ለመቀነስ ነው ተብሏል፡፡