በአገር ውስጥ እና በውጪ ለሚኖሩ፣ በጦርነት፣ በድህነት እና በረኀብ ለተጎዱ፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሶሪያውያን መርጃ የሚውል፣ የ10ነጥብ3 ቢሊዮን ዶላር ርዳታ እንደሚሰጡ፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች ይፋ አደረጉ።
በአውሮፓ ኅብረት አስተናጋጅነት፣ በብራስልስ በተካሔደው እና በሶሪያ ጉዳይ ላይ አተኩሮ በተካሔደው ዓመታዊ ጉባኤ፣ 57 ሀገራት እና 30 ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ርዳታ ለመስጠት የተስፋ ቃል ገብተዋል፡፡ ይኹንና መጠኑ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያስፈልጋል ካለውና ጥሪ ካደረገበት የርዳታ ገንዘብ፣ በ800 ሚሊየን ዶላር ያነሰ እንደኾነ ታውቋል።
በባለ27 አገራቱ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት ለሙሉ ቀን የተካሔደውን ጉባኤ፣ በማጠቃለያ ንግግር የዘጉት የኅብረቱ የሰብአዊ ርዳታ ኮሚሽነር ያኔዝ ሌናቺች፣ “ይህ ጉባኤ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፥ ከሶሪያ ሕዝብ ጎን መቆሙን የሚረጋግጥ ተጨባጭ ማሳያ ነው፤” ብለዋል።
በርዳታ እና በብድር የሚሰጠው ገንዘብ በጠቅላላው፣ ባለፈው ዓመት ቃል ከተገባው በ875 ሚሊዮን ዶላር እንደሚበልጥ የተናገሩት ሌናቺች፣ አክለውም፣ “ቀጥተኛ ንጽጽር” ማድረግ ግን እንደሚያዳግት ተናግረዋል። ለዚኽም ምክኒያቱ፣ ቃል የሚገባው ገንዘብ፣ በዓመታት ውስጥ የሚሰበሰብና በልዩ ልዩ ተቋማት አማካይነት የሚሰራጭ በመኾኑ፣ እንዲሁም የዋጋ ግሽበት እና የገንዘቡ የመግዛት ዐቅም፣ መጠኑን ከመወሰኑ ባሻገር፣ በከፊልም ደግሞ ሊከሠት መቻሉ እንደኾነ ጨምረው አስረድተዋል።