በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአማራ ባሕር ዳርና በኦሮምያ የተለያዩ ከተሞች ብዙ ሕይወት ጠፋ


ኦሮምያ ውስጥ ከሰላሣ በላይ፤ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባሕር ዳር ላይ ደግሞ ሰባት ሰው መገደሉ ተገለፀ፡፡

በአማራ ባሕር ዳርና በኦሮምያ የተለያዩ ከተሞች ብዙ ሕይወት ጠፋ
please wait

No media source currently available

0:00 0:31:08 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

ኦሮምያ ውስጥ ትናንት ቅዳሜና ዛሬ በተካሄዱ ግጭቶች ከ30 በላይ ሕይወት መጥፋቱን የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ - ኦፌኮ አስታወቀ፡፡

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ግድያዎቹ የተፈፀሙት በአሥራ አምስት የኦሮምያ ከተሞች ውስጥ እንደሆነ ከተሞቹን በስም፤ በየከተማው የደረሰውን ጉዳትም በቁጥር እየጠሩ ዘርዝረዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት ለሰልፎች ዕውቅና ባለመሥጠት ጥያቄዎቹን እንደሚያፍኑ የተናገሩት አቶ ሙላቱ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኦሮምያ ፕሬዚዳንትና አማካሪዎቻቸው የሰዉ ደም መፍሰስና ግጭቱ ከማንም በላይ ሊያሳስባቸው ይገባል” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ ባሕር ዳር ከተማ ላይ በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ሰባት ሰው መገደሉን የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አመልክተዋል፡፡

ፓርቲው ቀደም ሲል ጠርቶት የነበረውን ሰልፍ ፍቃድ ባለማግኘቱና ሊደርስ ይችላል ያለውን መዘዝ በመሥጋት መሠረዙን ትናንት አስታውቆ እንደነበር የገለፁት ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ነገሠ ተፈረደኝ ሰዉ በራሱ አደባባይ መውጣቱንና ቁጥሩም ምናልባት ጎንደር ላይ ወጥቶ ከነበረው ሰልፈኛ ሳይበልጥ እንደማይቀር አመልክተዋል፡፡

ባሕር ዳር ላይ የተገደሉት ሰባት ሰዎች መሆናቸውን ያረጋገጡት የክልሉ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከሰልፈኞቹ መካከል ፈንጂና ቦምብ የያዙ ነበሩ፤ እነዚሁ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎችና በተለያዩ ተቋማት ላይ ጥቃት ፈፅመዋል፤ የመንግሥት ኃይሎች ሕግ የማስከበር እርምጃ ወስደዋል” ብለዋል፡፡

በዚሁ ግጭት ወቅት ከሃምሣ በላይ ሰው መቁሰሉ ተገልጿል፡፡

መንግሥት የኃይል እርምጃ መውሰድ እንዲያቆም ያሳሰበው የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት የባሕር ዳሩን እርምጃ እንደሚያወግዝ አስታውቋል፡፡

የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ሃገሪቱን ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ ሊወስዳት እንደሚችል አሳስበዋል፡፡

በትናንትና በዛሬ የአማራና የኦሮምያ ክልሎች ሁኔታዎች ላይ የተቀናበሩትን ዘገባዎች ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG