በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በዩጋንዳው ፍንዳታ የተጠረጠሩት አራት ኢትዮጵያዊያን በነጻ ተለቀቁ


ፍንዳታውን አድርሰዋል የተባሉት አጥፍቶ ጠፊዎች ምስል
ፍንዳታውን አድርሰዋል የተባሉት አጥፍቶ ጠፊዎች ምስል

የዩጋንዳ ፖሊስ ፍንዳታውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ጥቃቶቹ በሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች መከናወናቸውን አስታውቆ፤ በጥርጣሬ የተያዙት ኢትዮጵያዊያን መለቀቃቸውን አረጋግጧል።

የፖሊሱ አዛዥ ካሌ ካይ-ሁራ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ በፍንዳታው ከተሰበሰቡት አስከሬኖች መካከል የሁለቱን ሬሳ ፈልጎ የመጣ ሰው አልተገኘም። የሁለቱን ሰዎች ማንነት የሚያሳዩ ምስሎችንም ፖሊስ አሳይቷል።

በአለም አቀፍ የወንጀለኛ አዳኝ ፓሊስ ኢንተር-ፖል ድረ ገጽ የሚገኙት እንደገና የተሰሩ ምስሎች የአጥፍቶ ጠፊዎቹን ማንነት ከሞላ ጎደል እንደሚያሳዩም ተጠቁሟል። አንደኛው ሰው ሶማሊያን ጨምሮ ከአፍሪካ ቀንድ ሰዎች የፊት ምስል ጋር የሚቀራረብ የቆዳ ቀለም ያለው ሰው ሲሆን፤ ሌላኛው ሰፋ ያለ ፊትና ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ነው።

የፖሊሱ አዛዥ ካሌ ካይሁራ እነዚህ ሰዎች የአጥፍቶ ጠፊዎች መሆናቸውን በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

“እነዚሁ ሁለት አስከሬኖች፤ ከሌሎቹ ሬሳዎች በተለየ መልኩ፤ መጥቶ ስጡን ያለ ሰው የለም። አሁን አንድ ሳምንት ሆኗል። ሁሉም አስከሬኖች በዘመድ ተለይተው ርክክብ ተደርጓል። እነዚህን የጠየቀ የለም፤ ይሄ ደግሞ አጋጣሚ ሊሆን አይችልም፣” ብለዋል።

ካይሁራ አክለውም የሰዎቹን ማንነት ለማወቅ አለም አቀፍ ዘመቻ መጀመሩን አስታውቀዋል።

“ኢንተር-ፖል፤ FBI እና ሌሎች አጋር የፖሊስ ሀይሎች ስራዮ ብለው ፍለጋውን ቀጥለዋል። ማንነታቸውን ማወቅ ለምርመራችን ወሳኝ ስለሆነ፤ በአለም ዙሪያ የነዚህን ሰዎች ማንነት እያስፈለግን ነው።”

ለዚህ ምርመራ የተለያዩ የፖሊስ ግብረ-ሀይሎች ወደ ካምፓላ አምርተዋል። የአሜሪካው የደህንነት ተቛም FBI ከ60 በላይ መርማሪዎቹን ልኳል። የዩጋንዳው እለታዊ ሞኒተር ጋዜጣም የኢትዮጵያ የደህንነት ሰራተኞችም ምክር እየሰጡ መሆናቸውን አስነብቧል።

የኢትዮጵያ ደህነንት ባለስልጣናት የካምፓላውን ፍንዳታ ያቀነባበረው ግለሰብ አሁንም አለመያዙን መጠቆሙን ዴይሊ ሞኒተር ጽፏል። የሰውየውን ማንነት ያልጠቀሱ መንጮችን የጠቀሰው ዘገባ ተጠርጣሪው የሶማሊያ ዜጋ መሆኑን አስነብቧል።

የዩጋንዳ ፖሊስ ከፍንዳታዎቹ ጋር በተያያዘ 20 ሰዎችን አስሯል። እነዚህም ዩጋንዳዊ፣ ፓኪስታናዊ፣ ኢትዮጵያዊና ሶማሊያዊ ዜግነት ያላቸው መሆናቸው ተጠቁሟል።

የፖሊስ አዛዥ ካሌ ካይሁራ ከነዚህ ሰዎች መካከል ተጠርጥረው የተያዙት ኢትዮጵያዊያን መፈታታቸውን ተናግረው፤ በፍንዳታው የውጭ ሀይሎች እጅ እንዳለበት ገልጸዋል።

“ከዚህ ፍንዳታ ጋር በቀጥታ የተገናኙ ሰዎችን መለየት የሚቻልበት ጊዜ ላይ አይደለግም። ገና ብዙ ስራ ይጠብቀናል በፍጥነት የምንናገረው የለም። መረጋገጥ ያለባቸው መረጃዎች አሉን። በነገራችን ላይ ፓኪስታናዊያን ብቻ አይደሉም፤ ከመካከላቸው ዩጋንዳዊያንም አሉበት።”

ለዚህ ፍንዳታ ሀላፊነቱን በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የእስልምና አክራሪ ቡድን አል-ሸባብ ሀላፊነቱን ወስዷል። አልሸባብ “ፍንዳታዎቹ የአፍሪካ ህብረት የሰላም አስከባሪዎች የሚገድሏቸው ሰዎችን ደም ይበቀላል” ማለቱ ይታወሳል።

ማለዳ ተፈተዋል የተባሉት ኢትዮጵያዊያን እስከ ሰኞ ማታ ድረስ በእስር መዋላቸውን በካምፓላ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አረጋግጠዋል።

XS
SM
MD
LG