የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የዘንድሮ ድርቅ ኢትዮጵያ ላይ ላደረሰው የምግብ እጥረት መቋቋሚያ ቀደም ሲል በሰጠው ገንዘብ ላይ 88 ሚሊየን ዶላር ተጨማሪ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኑ ተዘግቧል።
በኤል ኒኞ ምክንያት ለተፈጠረው ዓለምአቀፍ ክስተት መጋፈጫ እንዲውል ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የሰጠችውን የአጣዳፊ ጊዜ እርዳታ የሰሞኑ ተጨማሪ ድጋፍ ወደ 435 ሚሊየን ዶላር አሳድጎታል። ይህ ከዘጠኝ ቢሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ የኢትዮጵያ ብር መሆኑ ነው።
ተጨማሪው ድጋፍ እንዲሰጥ ያስፈለገበትን ምክንያት ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ያብራሩት በዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ የልማት ኤጀንሲ - ዩኤስኤአይዲ የባሕር ማዶ አደጋዎች ድጋፍ ቢሮ ኃላፊ ጀረሚ ካናንዳይክ “እያደገ የመጣውን የምግብ ዋስትና ፈተና በመገንዘባችን ነው” ብለዋል።
አሜሪካ ከጥቂት ቀናት በፊት ያደረገችው ተጨማሪ እርዳታ የመጨረሻው አለመሆኑን ሚስተር ካናንዳይክ ጠቁመው “ወደ አዲሱ የአውሮፓ 2016 ዓ.ም እየዘለቅን ስንሄድ ተጨማሪ ድጋፍ የምንሰጥ ይመስለኛል፤ እስከአሁን የሰጠነው እንደቅድሚያ ክፍያ እንዲሆን ነው፤ ያ ፍላጎት በዓመቱ ውስጥ እንዴት እየተለዋወጠ እንደሚሄድ ባየንና ግልፅ መረጃዎችን ባገኘን መጠን የምንሰጠውን ተጨማሪ ገንዘብ እናሣውቃለን” ብለዋል።
ወደ አዲሱ የአውሮፓ 2016 ዓ.ም እየዘለቅን ስንሄድ ተጨማሪ ድጋፍ የምንሰጥ ይመስለኛልበዩናይትድ ስቴትስ ዓለምአቀፍ የልማት ኤጀንሲ - ዩኤስኤአይዲ የባሕር ማዶ አደጋዎች ድጋፍ ቢሮ ኃላፊ ጀረሚ ካናንዳይክ
ካናንዳይክ በተጨማሪም “ጉዳዩን ትኩረት በጣም ሰጥቶ ከያዘው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርብ እየተጋገዝን መሥራታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።