በዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ኢህአዴግን ሙሉ በሙሉ አሸናፊ ያደረገውን የ2002ቱን ብሄራዊ ምርጫ ሂደትና ውጤት በመቃወም፥ ዩናይትድ ስቴትስ ኢትዮጵያን አስመልክቶ የምትከተለውን ፖሊሲ እንድትቀይር ለመጠየቅ ዛሬ በውጭ ጉዳይ ሚንስቴርና በዋይት ሃውስ ደጃፍ ሰላማዊ ሠልፍ አድርገዋል።
«ቃልዎን ይጠብቁ።» ሲሉ የዩናይድ ስቴትሱን ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማን ያሳሰቡት ሠልፈኞች «ነፃነትና ዲሞክራሲ በሌለባት ኢትዮጵያ ሠላም የለም።» የሚሉ መፈክሮችንም ሲያሰሙ ተደምጠዋል።
ሠልፉ፥ «የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መስሪያ ቤት በቅርቡ ያወጣውን መግለጫ በመደገፍና በተጨባጭ የፖሊሲ ለውጥ ዕርምጃዎች እንዲታገዝ ለመጠየቅ የተዘጋጀ ነው፤» ያሉት ከአስተባባሪዎች አንዱ ዶ/ር ካሳ አያሌው ናቸው።
ለውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሄላሪ ክሊንተን እንዲደርስ የተፃፈውና ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ዕጅ የገባው ደብዳቤ፥ “ገዢው ፓርቲና አጋሮቹ 99.6 በመቶውን የአገሪቱን ሸንጎ መቀመጫዎችና የክልል ምክር ቤቶችን ሙሉ መቀመጫዎች የተቆጣጠሩበት፥ ”በእጅጉ የተዛባ፤” ያለው ምርጫ ውጤት፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከታዩ ሌሎች “የተዛቡና የተጭበረበሩ ምርጫዎች፤” አንፃር እንኳን ሲታይ፥ ወደር የማይገኝለት አሳዛኝ የምርጫ ታሪክ የተዘገበበት ነው፤ ሲል ኮንኗል።
«በኢትዮጵያ ከአምባገነን አገዛዝ ወደ መልካም አስተዳደር ሰላማዊ ሽግግር ይደረግ ዘንድ፤ ዩናይትድ ስቴትስ በዲፕሎማሲያዊም ሆኑ በሌሎች መንገዶች ግፊት እንድታደርግ፤» ሲል የቀረበው ይህ ደብዳቤ፣ «በዚያች አገርና በአካባቢው አገሮች ዕውነተኛ፥ ዘላቂና አስተማማኝ ሰላም ሊመጣ የሚችለው፥ ከኢትዮጵያ ኅዝብ ወገን እንጂ ኅዝቡን ከሚጨቁን ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ጎን ሲሰለፉ አይደለም፤» ሲል የዩናይትድ ስቴትስን መንግስት አሳስቧል።
ደብዳቤውን ከተቀበለው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴርም ሆነ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ሰልፉን አስመልክቶ ለጊዜው የተሰጠ አስተያየት የለም።
“March for Freedom” የተባለው የፖለቲካና የማኅበራዊ ለውጥ አቀንቃኝ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን አሜሪካውያን የተሰባሰቡበት ቡድን በጠራው በዚህ ሠልፍ በመቶዎች የሚገመት ኅዝብ ተሳትፏል።