በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በማጀቴ ከ30 ያላነሱ ንጹሐን ዜጎች በመከላከያ ኀይሉ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ተገለጸ


በማጀቴ ከ30 ያላነሱ ንጹሐን ዜጎች በመከላከያ ኀይሉ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:56 0:00

በማጀቴ ከ30 ያላነሱ ንጹሐን ዜጎች በመከላከያ ኀይሉ የቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ተገለጸ

የኢትዮጵያ መከላከያ ኀይል ወታደሮች፣ በዐማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ማጀቴ ከተማ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ ባካሔዱት የቤት ለቤት ፍተሻ፣ 30 የሚደርሱ ንጹሐን ዜጎችን እንደገደሉ፣ ሮይተርስ ስድስት የአካባቢ ነዋሪዎችን በእማኝነት ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ የፌዴራል ኀይሎቹ፣ ከአንድ ወር በላይ ለሚኾን ጊዜ፣ ከዐማራ ክልል ታጣቂዎች ጋራ በሚያደርጉት ፍልሚያ ጥቃት እንደደረሰባቸው በዘገባው ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል መንግሥት እና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃል አቀባዮች፣ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ፣ ሮይተርስ ባለፈው ዐርብ ቢጠይቃቸውም ምላሽ አላገኘም።

ሊደርስባቸው የሚችለውን አጸፋ በመፍራት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የማጀቴ ከተማ ነዋሪ ለሮይተርስ ሲናገሩ፣ ሕይወታቸው ካለፉት ሰዎች መካከል፣ ሕፃናት እና አዛውንቶች ይገኙበታል፤ አንዳቸውም ግን በሚሊሺያ ቡድን ውስጥ እንዳልተሳተፉ አመልክተዋል።

ከነዋሪዎቹ አንዱ፣ ወታደሮቹ ወንድሙን ሲገድሉ እንደተመለከተ ገልጿል፡፡ ሌሎች ነዋሪዎች ደግሞ፣ ፍተሻው በቀጠለበት ወቅት የተኩስ ድምፅ እንደሰሙና የግድያውን አፈጻጸምም ከጎረቤቶቻቸው እንደተረዱ ተናግረዋል። ሮይተርስ፣ የነዋሪዎቹን መግለጫ ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።

በሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ፣ በዐማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ የፌዴራል ኀይሎች ጥቃት እንደፈጸሙ ስለሚቀርበው ክሥ፣ መንግሥት እስከ አሁን በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም። ኾኖም፣ ከዚኽ ቀደም በአጎራባቹ የትግራይ ክልል በተቀሰቀሰው ግጭት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይሎች፣ ሰብአዊ መብቶችን እንደሚያከብሩ መግለጹ ይታወሳል።

የማጀቴ ከተማ ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ ከሮይተርስ ጋራ ባደረጉት የስልክ ቃለ ምልልስ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ የፋኖ ታጣቂዎች በከተማው በነበሩ የመከላከያ ኃይሎች ላይ ጥቃት አድርሰዋል፡፡ ሁለቱ ተፋላሚዎች ለተወሰኑ ሰዓታት ያደረጉት ውጊያ ከበረደ በኋላ፣ ወታደሮቹ የቤት ለቤት ፍተሻውን ማካሔድ ጀምረዋል።

በዚኽም፣ 29 እና 30 የሚደርሱ ነዋሪዎች በወታደሮቹ እንደተገደሉ፣ ብዙዎቹ ማቾች በተቀበሩባቸው አብያተ ክርስቲያናት የሚያገለግሉ ሁለት ቀሳውስት እና የከተማው ነዋሪዎች ለሮይተርስ ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል ሦስቱ ለሮይተርስ ሲገልጹ፣ ንጹሐኑ ዜጎቹ የተገደሉት በጥይት ተደብድበው ነው፡፡ ሌሎች ሦስት ነዋሪዎች በአንጻሩ፣ ሰዎቹ ምናልባት ወታደሮቹን ለመደገፍ ወደ ማጀቴ ከመጡ የሌላ ብሔረሰብ ሰዎች ተገድለው ይኾናል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

“እናት” የተሰኘው ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ባለፈው ሳምንት እሑድ፣ በማጀቴ ከተማ በተካሔደ የቤት ለቤት ፍተሻ፣ ወታደሮች፣ 29 ሰላማዊ ዜጎችን ያለርኅራኄ ገድለዋል፤ ብሏል።

ሮይተርስ ያነጋገረው አንድ ሌላ የከተማዋ ነዋሪ፣ ስምንት እና ዘጠኝ የሚደርሱ የመከላከያ ኃይሎች ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች፣ የቤተሰቦቹን መኖሪያ ግቢ ጥሰው ከገቡ በኋላ፣ የ62 ዓመት ወንድሙን ሲገድሉ እንደተመለከተ ገልጿል።

“ወንድሜ ከውጭ የሰዎች ንግግር ሲሰማ፣ ጎረቤቶቻችን መስለውት ነበር፤” ያለው ይኸው ነዋሪ፣ “በእጁ ምንም አልያዘም ነበር። ከበሩ አጠገብ ቆሞ እነርሱ በሩን ጥሰው ገብተው ከኋላው በጥይት መቱት፤” ብሏል።

በየቦታው የሚፈሰው ደም

አንድ ሌላ ነዋሪ፣ ወታደሮቹ የ29 ዓመት ወንድሙን፣ በቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤት በር ላይ እንደገደሉት ይናገራል። “ሚስቱ እየሮጠች ወደ እኛ መጣች። ቤቴ ከእርሱ ቤት ምናልባት 15 ሜትር ርቀት ላይ ነው። እንደደረሰች፣ በጥይት መቱት፤ አለችን፤” የሚለው ይኸው ነዋሪ፣ “ደሙ በየቦታው ፈሶ ነበር፤ ነገር ግን ድምፅ ማሰማት አንችልም ነበር። ስለዚህ ድምፃችንን ሳናሰማ እያለቀስን ነበር፤” ሲል ኹኔታውን አስረድቷል።

በማግስቱ ወታደሮች ከአንድ ከፍተኛ መኰንን ጋራ ኾነው የማጀቴን ነዋሪዎች እንደሰበሰቧቸው የገለጹት አስተያየት ሰጪዎቹ፣ ስብሰባውን ከተካፈሉት ነዋሪዎች አንዱ፣ “መኰንኑ፥ ጥቃት ያደረሱባቸውን ሰዎች ማግኘት እንዳልቻሉ ሲናገር ነበር። ከዚኽ በኋላ አንድ ጥይት ብትተኩሱ እናጠፋችኋለን ብሏል፤” ሲል ለሮይተርስ ተናግሯል።

በዐማራ ክልል የተስፋፋው ግጭት የተቀሰቀሰው፣ የፌዴራል ባለሥልጣናት የክልሉን ደኅንነት ለመሸርሸር እየሞከሩ ነው፤ በሚል ቅሬታ ሲኾን፣ መንግሥት ግን ክሡን አይቀበልም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት፣ በዐማራ ክልል በተስፋፋው ግጭት እስከ አሁን ድረስ ቢያንስ 183 ሰዎች እንደተገደሉ አስታውቆ፣ ኹሉም ወገኖች፣ ግድያንና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰትን እንዲያቆሙ ጥሪ አድርጓል።

በዐማራ ክልል ግጭቱ ከተነሣበት ጊዜ አንሥቶ፣ በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ፣ ነዋሪዎች የገለጿቸውን በርካታ ክሥተቶች ማረጋገጥ አስቸጋሪ ኾኗል።

የክልሉ ጦርነት የተቀሰቀሰው፣ መነሻውን በትግራይ ክልል ያደረገውና በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የተካሔደው የእርስ በርስ ጦርነት ካበቃ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በሰሜኑ ግጭቱ የተካፈሉ ሁሉም ወገኖች፣ “በሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ወንጀል” ሊባሉ የሚችሉ የመብቶች ጥሰትን እንደፈጸሙ አስታውቆ ነበር።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ኾነው የተዋጉት የፋኖ ታጣቂዎች፣ አሁን በዐማራ ክልል በተስፋፋው የትጥቅ ግጭት፣ የፌዴራል ኃይሎች ገፍተው እስኪያስወጧቸው ድረስ፣ የክልሉን ዋና ዋና ከተሞች መቆጣጠር ችለው ነበር። በየከተሞቹ ዙሪያ እና ራቅ ባሉ አካባቢዎች ግን፣ የትጥቅ ግጭቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።

በሮይተርስ የተጠናቅረውን ዘገባ ስመኝሽ የቆየ ወደ ዐማርኛ መልሳዋለች።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG