በሕገወጥ መንገድ ተታልለው ከሃገር ከወጡ በኋላ በታንዛኒያ እሥር ቤቶች ውስጥ ቆይተው እንደነበር የገለፃቸውን 435 ኢትዮጵያዊያን ፍልሰተኞች ወደ ሃገር እየመለሰ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል፡፡
ናይሮቢ በሚገኘው በኬንያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዳያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስትር ካውንስለር አቶ መለስ ዓለም ለቪኦኤ በሰጡት መግለጫ መሠረት የመጀመሪያው ቡድን አባላት የሆኑት 253 ተመላሾች ዛሬ፤ ዓርብ ከቀትር በኋላ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ ወደሃገራቸው እየተመለሱ ያሉት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የታንዛኒያ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና አዲስ አበባ የሚገኘው የዓለምአቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች - አይኦኤም የኢትዮጵያ ቢሮ በጋራ ባደረጉት ጥረት መሆኑን የኤምባሲው ሪፖርት አስታውቋል፡፡
ኬንያ የሚገኘውና ታንዛኒያን ጨምሮ ሌሎችንም የአካባቢውን ሃገሮች የሚሸፍነው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባለሥልጣናት ታንዛኒያ ሄደው የዜግነት ማጣራት ማድረጋቸውንና ኢትዮጵያዊያኑ የአንድ ዓመት የእሥር ጊዜያቸውን የጨረሱ፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፍርድ ያልቀረቡ፣ ገሚሶቹም የፍርድ ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በተደረገ ጥረት በታንዛኒያ መንግሥት ምኅረት የተደረገላቸው መሆናቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
ዕድሜአቸው ከ15 እስከ 39 ዓመት የሆነና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሃድያ እና ሆሣዕና አካባቢ የመጡት ኢትዮጵያዊያን እንደገለፁት ከእነርሱ ጋር ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ በሚል ከተነሱ ውስጥ መንገድ ላይ ሕይወታቸው ያለፈና አካላቸው የጎደለ ብዙዎች እንዳሉ መናገራቸውን ኤምባሲው በዚሁ መግለጫው ላይ አስፍሯል፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ ከሃገር ለመውጣት ከ50 ሺህ እስከ 70 ሺህ ብር ለሕገወጥ አሸጋጋሪዎቹ መክፈላቸውን እንደገለፁለት ኤምባሲው ጠቁሟል፡፡
አቶ መለስ ዓለም ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ለመስማት የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ይክፈቱ፡፡