በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በሶማሊያ


ሶማሌላንድ እና ፑንትላንድ
ሶማሌላንድ እና ፑንትላንድ

ሶማሊያ ውስጥ በሶማሌላንድ እና በፑንትላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉይይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የአካባቢው ተጠሪዎችና በአካባቢውም ባለሥልጣናት በደል እየደረሰባቸው መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለፁ ነው፡፡

በሁለቱም አካባቢዎች የሚኖሩት ስደተኞች ሙሉ ሕይወታቸው በችግርና በመከራ የተጣበበ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ከስደተኞቹ እና ከባለሥልጣናቱም ጋር እየተነጋገረ ያለው ሰሎሞን አባተ ለዛሬ ተከታዩን ዝግጅት አሠናድቷል፡፡

ቦሣሶ - ፑንትላንድም ሆነ በሶማሌላንዷ ሃርጌሣ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከፍትሕ መዛባት ጀምሮ በመንግሥታቱ ድርጅት በቂ ጥበቃና ድጋፍ እንደማይደረግላቸው እንዲያውም ጥቃት እንደሚደርስባቸው ነው የሚናገሩት፡፡

ባለፈውም ሣምንት በቦሣሶ ብሦታቸውን ለማሰማት ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የቦሳሶ ቢሮ በሄዱ ስደተኞች ላይ የመሥሪያ ቤቱ የጥበቃ ሠራተኞች ድብደባ ማድረሣቸውና የታሠሩም እንዳሉ ተሰምቷል፡፡

ቀደም ባለ አንድ ዝግጅት የቦሣሶ ስደተኞችን ሕይወት፣ የፍትሕና ጥበቃ ማጣት ብሶታቸውን መመልከት ጀምረናል፡፡ የአካባቢውን ባለሥልጣናትና የዩኤንኤችሲአርንም ኃላፊዎች ለማነጋገር በተደጋጋሚና በየአጋጣሚውም ሙከራዎችን እያደረግን ነው፡፡

ከትናንት በስተያ ባስተላለፍነው በሐርጌሣ ሶማሊላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ሕይወት ላይ ከስደተኞቹ አንዱ ያሰሙትን ብሶት በከፊል አስደምጠናል፡፡ ይህንንና ወደፊትም የምናቀርባቸውን ጥያቄዎቻቸውን ይዤ ሃርጌሣ ለማገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ተጠሪ ፅ/ቤት ኃላፊ ለሚስተር አብዱላሂ ባሬ ደውዬ አነጋግሬአቸው ነበር፡፡

ሚስተር አብዱላሂ በአሁኑ ጊዜ በሃርጌሣ 1600 የሚሆኑ የተመዘገቡ ስደተኞች እንደሚገኙና ወደ 98 ከመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊያን ቀሪዎቹ ደግሞ ኤርትራዊያን መኖናቸውን እንዲሁም ወደ ሃያ ሺህ የሚሆኑ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎች መኖራቸውን ነግረውኛል፡፡

መሥሪያ ቤቱ ለሕፃናቱ የትምህርት ቤት ወጭና ለታመሙ ደግሞ የሕክምና ድጋፍ እንደሚሰጡ ሚስተር አብዱላሂ ገልፀዋል፡፡ እስካለፈው ታኅሣስ መጨረሻ አካባቢም የገንዘብ ድጋፍ ይሰጡ እንደነበርና ከአውሮፓዊያኑ 2010 ማብቂያ በኋላ ጄኔቫ በሚገኘው የኮሚሽነሩ ዋና ፅ/ቤት መመሪያ የገንዘብ ድጋፍ ማቆሙን፤ ድጋፍ የሚያገኙት የከበደ ችግር ያለባቸው ብቻ መሆኛቸውን አመልክተዋል፡፡

በሚስተር አብዱላሂ አባባል አሁን ከ1600ው የገንዘብ ድጋፍ የሚሰጣቸው 160 ስደተኛ ቤተሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ “ቀሪዎቹ ግን - አሉ ማስተር አብዱላሂ፡-

“እኛ የአንዳንድ ተለዋጭ ሥራዎችን ሃሣብ አቅርበንላቸዋል፡፡ ለመሥራት የሚችሉትን ሃሣብ እያቀረቡ የመነሻ ገንዘብ እንሰጣቸዋለን፡፡ የገቢ ማስገኛ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ ለዚህም ገንዘብ ለማግኘት ከዓለምአቀፎቹ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከአንዱ ጋር ተደራድረናል፡፡ ከዚያ የምናገኘውን ገንዘብ ለእነርሱ ለገቢ ማስገኛ ሥራቸው እንሰጣቸዋለን፡፡”

የስደተኞቹ ችግር ተደራራቢ ነው፡፡ አንድም እንዲሁም ለግለሰብ አርባ፣ ለቤተሰብ ስድሣ ዶላር በወር ይሰጣቸው የነበረው ገንዘብ እጅግ አነስተኛ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን ችግሩ ባሰ ይላሉ ስደተኞቹ፡፡

የዩኤንኤችሲአር ሃርጌሣ ቢሮ ኃላፊ የሚናገሩት ዓይነት ገቢ ማስገኛ የሚባለው የሥራ ሃሣብ በሃርጌሣ ጨርሶ እንደማይሠራ ነው ስደተኞቹ የሚናገሩት፡-

የስደተኞች ጉዳይ ፅ/ቤቱ ኃላፊ አብዱላሂ ዋዴ ግን የሚሉት ማንም አልሞከረውም ነው፡፡

“በርግጥ በሌላ ሃገር ውስጥ ከሕዝቡ ጋር ለመቀላቀል፣ ስኬታማ ንግድ ለመሥራት ቀላል አይሆንም፡፡ ይሁን እንጂ ቢያንስ እንሞክረው - ይላሉ አብዱላሂ - የመሞከር፣ ሥራ የመሥራት ዕድል ተከፍቶላቸዋል፡፡" አዲሱ የሶማሊላንድ መንግሥት እነርሱን ለማስተናገድ ደስተኛ መሆኑን፣ ሥራም መሥራት እንደሚችሉ በዩኤንኤችሲአር ፊት ያረጋገጠላቸው መሆኑንና ዓለምአቀፍ የደህንነት ከለላም እንደሚሰጧቸው ባለሥልጣናቱ መናገራቸውን የዩኤንኤችሲአሩ የሃርጌሣ ተጠሪ አመልክተዋል፡፡ "እየሞከሩ፣ ይህንን እራሣቸውን የመደገፍ ሥራቸውን እየሠሩ ችግር ሲገጥማቸው የስደተኞችን ደሕንነት የመጠበቅ ዓለምአቀፍ ግዴታ እንዳለባቸው፤ የስደተኞቹንም መብቶች አንስተን እናሳስባቸዋለን፡፡” ብለዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት በመሠረቱ የሚያከናውናቸው ተግባራት ሦስት መሆናቸውንና እነርሱም ስደተኞችን ወደሌላ አካባቢ መላክ፣ ወይም ወደመጡባቸው ሥፍራዎች እንዲመለሱ ማድረግና ባሉባቸው የስደት ሥፍራዎች ተቀላቅለው እንዲኖሩ ማስቻል መሆናቸውን ስደተኞቹ ይናገሩና፣ ይህ የሚሆነው ግን በስደተኞች ትብብርና መልካም ፍቃድ ላይ ተመሥርተው እንጂ በኃይል አይደለም ይላሉ፡፡

በሶማሊያ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች የሚናገሯቸው ችግሮች በጣም ስፋት ያላቸው ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ብሶቶቻቸው፣ በየደረጃው ያሉት የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ መሥሪያ ቤት እና የየአካባቢውም ባለሥልጣት መልሶች በተከታታይ ክፍሎች ይቀርባሉ፡፡

ለዝርዝርና ለተጨማሪ መረጃ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG