ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በኬንያ ጉብኝታቸዉ ለ3 ቀናት እንደሚቆዩ ተገልጿል። ናይሮቢ ሲገቡ አቀባበል ያደረጉላቸዉ የኬንያ ምክትል ፕረዝደንት ዊልያም ሩቶ ናቸዉ። ትላንት ማታም ከኬንያዉ ፕረዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ጋር በኬንያ ብሔራዊ ቤተ- መንግስት ተገናኝተዉ ሠፊ ወይይት አድርገዋል። ሁለቱ መሪዎች ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ኬንያና ኢትዮጵያ ስምምነቶች መፈራረማቸዉን አረጋግጠዋል። ስምምነቶቹም በማዕድን ማዉጣት፣ በጤና፣ በስፖርት፣ በህገወጥ የሰዎች ዝዉዉርና በትምህርት ዘርፍ ሲሆኑ፣ ሌላዉ ደግሞ በአይነቱ ልዩ የሆነ የንግድ ስምምነት መፈራረማቸዉን የኬንያዉ ፕረዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ተናግረዋል።
ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመቻቸዉን ስምምነቶች ኢትዮጵያን በመወከል የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ የትራንፖርት ሚኒስትሩ አቶ ገበየሁ ወርቅነህ፣ የማዕድንና ኢኔርጂ ሚኒስትሩ አቶ ቶሎሳ ሻጌና የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትሩ አቶ ስለሺህ ጌታሁን ስምምነቶቹን ተፈራርመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር የጥንት ወዳጅ ናት ብሎአል።
‘ኬንያንና ኢትዮጵያ አንድ የሚያደርጋቸዉ ብዙ ነገር አላቸዉ፣ ፕረዝደንቱ እንዳሉት አካካቢያችንን ሰላማዊ ለማድረግ መሥራት አለብን፣ ይህ አካባቢ ሰላማዊ ሆኖ ለንግድ፣ ለኢንቨስትመንትና ቱሪዝም አመቺ እንዲሆን ማድረግ የሚችሉት ኢትዮጵያና ኬንያ ብቻ ናቸዉ። ስለዚህም ዛሬ የተፈራረምናቸዉ ስምምነቶች ይሄ ዓላማ እንዲሳካ ጥሩ ግብዓት ይሆናሉ፣ ይህ ስምምነት እዉን እንዲሆን የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ ያደረጉ በተለይ የፕረዝደንቱ ልኡካንን ከልብ ማመስገን እፈልጋለሁ። በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያለዉን ትብብር የተሻለ ለማድረግ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ ናት።’
ከስምምነቶቹ መካከል ከኬንያ የድምበር ግዛት ለሙ እስከ አዲስ አበባ ሊዘረጋ የታሰበዉ የተፈጥሮ ጋዝ ቱቦ መስመር ትልቁ ሲሆን ኬንያና ኢትዮጵያ በዚህ በ2016 ዓ.ም መጨረሻ ስምምነቱ ወደ ተግባር የሚቀይር ሌላ ስምምነት እንደሚፈራረሙ የኬንያ ቤተ መንግስት በሰጠዉ መግለጫ አሳዉቋል። በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የፕሮጀክቱን አተገባበር በተመለከተ ማብራርያ ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈዉ ሚያዝያ ወር በኦሞ ወንዝ ላይ ግልገል ጊቤ ቁጥር አራት የኃይድሮ ኤለክትሪክ ማመንጫን ለመገንባት ያሳወቀች ስትሆን የፕሮጀቱ መገንባት በሰሜን ምዕራብ ኬንያ የሚገኘዉን ቱርካና ኃይቅ ያደርቃል በማለት የኬንያ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሃመድ ከሳምንት በፊት ‘ዘ ስታር’ ለተባለ የኬንያ ጋዜጣ ተናግረዉ ነበረ። እንደያኔዉ ዘገባ ኬንያ ስለ ግልገል ጊቤ ቁጥር አራት ለኢትዮጵያ አቤት እያለች መሆኑ የተነገረ ሲሆን ትላንት የሁለቱ ሃገሮች የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሲገናኙ ኬንያ ይህንን ጥያቄ አቅርባ ነበር ወይ ተብለዉ አምባሳደር ዲና ተጠይቀዉ፣ ይህ ጥያቄ በሁለቱ ሃገር መሪዎች መካከል አልነበረም ብለዋል።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።