የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሥልጣን ከተረከቡ የመጀመሪያ የውጭ ጉዟቸውን ዛሬ ወደ ጂቡቲ አድርገዋል።
የጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ጂቡቲ-አምቦሌ ዓለምአቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ላይ ተገኝተው ተቀብለዋቸዋል።
"የሁለቱ ሃገሮች ግንኙነት ከሁለት ሃገርነትና ከጉርብትና ሌላ ቤተሰባዊም ጭምር ነው" ብለዋል ከልዑካን ቡድኑ ጋር ጂቡቲ የሚገኙት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ለቪኦኤ በሰጡት ቃል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጂቡቲ የገቡት ግዙፍ የተባለ የመንግሥታቸውን ልዑካን ቡድን መርተው ሲሆን በሁለት ቀናት የጂቡቲ ቆይታቸው ወቅት በፀጥታ፣ በልማት፣ በንግድና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ እንደሚመክሩ ለጂቡቲ መንግሥት ቅርበት ያላቸውን የቪኦኤ ምንጮች የጠቀሰ እዚያው ጂቡቲ የሚገኝ የሶማሊኛ ዝግጅት ክፍላችን ሪፖርተር ዘግቧል።
ከልዑካኑ መካከል የኢትዮጵያውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንትን ማየቱን ሪፖርተሩ ገልጿል።
የሁለቱ ሃገሮች ከፍተኛ ልዑካን በነገው ዕለት የስምምነት ሰነዶችንም እንደሚፈራረሙ ተገልጿል።
የጂቡቲው ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያውን መሪ ከተቀበሉ በኋላ ለእራት ወደ ቤተመንግሥታቸው ይዘዋቸው ሄደዋል።
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ