በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጀልባ መገልበጥ አደጋ ቢያንስ የ21 ኢትዮጵያውያን ሕይወት አለፈ


በጀልባ መገልበጥ አደጋ ቢያንስ የ21 ኢትዮጵያውያን ሕይወት አለፈ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:58 0:00

በጀልባ መገልበጥ አደጋ ቢያንስ የ21 ኢትዮጵያውያን ሕይወት አለፈ

ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን አሳፍራ ወደ ጅቡቲ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ ተገልብጣ፣ ሕፃናትንና ሴቶችን ጨምሮ ቢያንስ 21 ኢትዮጵያውያን መሞታቸውን፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM) ገልጿል፡፡

አደጋው የደረሰው፣ ትላንት ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም. ምሽት ላይ፣ ወደ ሳዑዲ አረቢያ መግባት የተሳናቸውን 77 ኢትዮጵያውያንን ከየመን የባሕር ዳርቻ አሳፍራ በመመለስ ላይ የነበረች ጀልባ፣ በጅቡቲ የባሕር ዳርቻ አካባቢ በመገልበጧ እንደኾነ፣ የፍልሰት ድርጅቱ የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬይ ቪራይ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በአደጋው መሞታቸው ከተረጋገጠው 21 ፍልሰተኞች በተጨማሪ ሌሎች 23 ኢትዮጵያውያንን እስከ አሁን ማግኘት እንዳልተቻለም ቃል አቀባዩ አመልክተዋል፡፡ በአሁኑ ሰዓት፣ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት የጅቡቲ መሥሪያ ቤት፣ ከጅቡቲ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እና ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋራ በመኾን፣ በአደጋው የጠፉትን ፍልሰተኞች የማፈላለግ ሥራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(IOM)፣ የሟቾቹ ቁጥር 16 እንደነበረና 28 ሰዎች ደግሞ እንዳልተገኙ፣ ዛሬ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ገልጸው ነበር፡፡ ኾኖም፣ የአይኦኤም የኢትዮጵያ ቃል አቀባይ ኬይ ቪራይ፣ የሟቾቹ ቁጥር ማሻቀቡን ምሽት ላይ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡ 33 ፍልሰተኞች ደግሞ ከአደጋው በሕይወት መትረፋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የምሽቱ የጀልባ መገልበጥ አደጋ የተሰማው፣ በተመሳሳይ ስፍራ በደረሰ መሰል አደጋ ቢያንስ 38 ኢትዮጵያውያን ሕገ ወጥ ፍልሰተኞች ከሞቱ ከኹለት ሳምንታት በኋላ ነው፡፡ ሁለቱም አደጋዎች የተከሠቱት፣ የተሻለ ሥራ እና ዕድል የማግኘት ተስፋ ሰንቀው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እየተጓዙ መድረስ ያልቻሉ ፍልሰተኞች፣ ከየመን ወደ ጅቡቲ በመመለስ ላይ እያሉ ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ የጠየቅናቸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ፣ በተደጋጋሚ እየተከሠተ ባለው መሰል አደጋ ላይ ብዙ ጊዜ አስተያየት እንደተሰጠ አውስተው፣ የትላንቱን የጀልባ አደጋም በተመለከተ ምንም ማለት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በተከሠተው ተመሳሳይ አደጋ ላይ በሰጡን አስተያየት፣ ከሳዑዲ አረቢያ ሕገ ወጥ ፍልሰተኞችን ለመመለስ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት የደረሰው ኅልፈት የችግሩን አስከፊነት የሚያሳይ ነው፤ ብለው ነበር፡፡

በሕገ ወጥ ጉዞው፣ ፍልሰተኞች የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የጥቅም ዒላማ ከመኾናቸው ባለፈ ለአፈና፣ የዘፈቀደ እስራት እና በየመን ተፋላሚ ቡድኖች ለግዳጅ የውጊያ ምልመላ እንደሚያጋለጡ፣ ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት በቅርቡ መግለጹም አይዘነጋም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG