የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የግንቦት አስራ አምስቱ ምርጫ እንደገና እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሰሙትን አቤቱታ ውድቅ አደረገ።
ፍርድ ቤቱ በዛሬ ውሳኔዉ፣ የታቃዋሚዎቹን ይግባኝ ውድቅ በማድረግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ አጽንቶታል። ምርጫው ተጭበርብሯል፣ ከድምጽ መስጪያዉ ቀን በፊት ጀምሮ መራጮችን ማስፈራራት ነበር በማለት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቡትን ስሞታ የምርጫ ቦርድ በማስረጃ አልተደገፈም ሲል ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም።
በምርጫው ውጤት መሰረት ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል፣ 547 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ሲያሸንፍ፥ የስምንት ፓርቲዎች ጥምረት መድረክ ግን አንድ መቀመጫ ነዉ ያሸነፈዉ።
የመድረክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቃዋሚዎችን ስሞታ በቁም ነገር ያዬዉ አይመስለንም ብለዋል። የእርሳቸዉ ፖርቲ መድረክ ለሰበር ችሎት ይግባኝ ሊል እንደሚችልም ጠቁመዋል።