በዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ ክትባት አሰጣጥ ሂደት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ክትባቱን ለማግኘት የተለያዩ መስፈርቶችና የጊዜ ቅደም ተከተሎች ያሉት ሲሆን እንደየ ክፍለ ግዛቶቹ ይለያያል፡፡ እዚህ ቨርጂኒያ ውስጥ ግን የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት ምንም ዓይነት ምዝገባና ወረፋ መጠበቅ ሳያስፈልጋቸው ከየትኛውም አካባቢ የመጡም ቢሆን፣ መታወቂያና የመድን ወይም ኢንሹራንስ ካርዳቸውን ብቻ በመያዝ ክትባቶቹ ወደሚሰጡበት ቦታ ሄደው ሲወስዱ ተመልክተናል፡፡
ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ ቨርጂኒያ ስፕሪንግ ፊልድ፣ ቫንዶርንና ፍራንኮንያ ላይ በሚገኘው አማኑኤል የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እና የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የልማት ድርጅት ኢሲዲሲን (ECDC) ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያውያን የንግድና የእምነት ተቋማት ውስጥ ክትባቱ ሲሰጥ መቆየቱንና በሌሎች ሥፍራዎች በቅርቡም የሚቀጥል መሆኑንም አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በርካታ በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵውያውይን የህክምና ባለሙያዎች የተሳተፉበትን የክትባቱን መርሃ ግብር ያቀናጀችው የፋርማሲ ባለሙያና የቫንዶርን መድሃኒት ቤት ባለቤት የሆነችው ዮዲት ጉልላት ለአሜሪካ ድምጽ እንደተናገረችው ካለፈው መጋቢት ጀምሮ እስካሁን ወደ 15ሺ የሚሆኑ ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ ማድረግ ተችሏል፡፡ የዛሬው ኢትዮጵያውን በአሜሪካ ፕሮግራማችን እንግዳችን አድርገናታል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡