በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የቴክኖሎጂ ሁለት ስለቶች - በኤልያስ ስሜ “የተወጠረ ገመድ”


የቴክኖሎጂ ሁለት ስለቶች - በኤልያስ ስሜ “የተወጠረ ገመድ”
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:30 0:00

የቴክኖሎጂ ሁለት ስለቶች - በኤልያስ ስሜ “የተወጠረ ገመድ”

በዩናይትድ ስቴትስ፣ ኮሎራዶ ግዛት በሚገኘው ዴንቨር የሥነ ጥበብ ሙዚየም፣ ዘመነኛ የጥበብ ሥራዎችን ያካተተ ጋለሪ በዚኽ ወር ሲከፈት፣ የጎብኚዎችን ቀልብ ከሳቡ የፈጠራ ሥራዎች መካከል አንዱ፣ “Tight Rope” (“የተወጠረ ገመድ”) የተሰኘውና ዓለም አቀፍ እውቅናን ባገኘው ኢትዮጵያዊ አርቲስት ኤልያስ ስሜ የተሠራው የጥበብ ውጤት ነው።

አገልግሎታቸውን ከጨረሱ የቴክኖሎጂ ቁሶች ተቀጣጥለውና ተወሳስበው የተሠሩት የኤልያስ የጥበብ ሥራዎች ከሩቅ ሲታዩ፣ መልክአ ምድርን ይመስላሉ፡፡ ኤልያስ እንደገለጸው፣ ቴክኖሎጂ ከሰው ልጅ ጋራ ያለውን ታሪካዊ ትስስር ያንጸባርቃሉ፡፡

በኮሎራዶ ግዛት፣ ዴንቨር ከተማ በሚገኘው፣ ዴንቨር የሥነ ጥበብ ሙዚየም፣ ዘመነኛ የጥበብ ሥራዎችን አካቶ የተከፈተው የሥነ ጥበብ ዐውደ ርእይ በሚታይበት አዳራሽ፣ በአንደኛው ግድግዳ እኩሌታ ላይ ያረፈው፣ የኤልያስ ስሜ የጥበብ ሥራ ቀልብን ይገዛል።

እንደ ኮምፒዩተር ቁልፎች፣ እናትቦርድ እና የኤሌክትሪክ ሽቦዎች የመሳሰሉ አገልግሎታቸውን የጨረሱ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶችን፣ በኢትዮጵያ ባህላዊ የሽመና ጥበብ በማዋሐድ እና ሽቦዎችን በማጠላለፍ የተሠራው ረቂቅ ጥበብ፣ ከርቀት ሲታይ የአንድ ከተማ ካርታ ይመስላል። ጠጋ ብለው ሲያዩት ደግሞ የተለያየ ቀለም ያላቸው የኤሌክትሪክ አስተላላፊ ሰሌዳዎቹ እና የተጠላለፉት የኤሌክትሪክ ሽቦዎች፣ የሰው ልጅ በየቀኑ የሚጠቀማቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እና በሕይወታችን ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ ያስታውሳሉ።

ኤልያስ “ታይ ሮፕ” ወይም የተወጠረ ገመድ በሚል ስያሜ የሚሠራቸው፣ በዐይነታቸው ለየት ያሉት እኒኽ የፈጠራ ሥራዎች፥ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውሮፓ እና በልዩ ልዩ የዓለማችን ክፍሎች በሚገኙ ሙዚየሞች ውስጥ የሚገኙ ሲኾን፣ እስከ 190 ሺሕ የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ ዋጋ አላቸው።

በዴንቨር ሥነ ጥበብ ሙዚየም የዘመናዊ ጥበብ ባለሞያ ሮይ ፓደከን ፣ የኤሊያስ ሥራዎች፥ ከጥበብ ባሻገር የሥነ ሕንፃ ዲዛይን ይዘትም እንዳላቸው ያስረዳሉ።

“የኤልያስ ሥራ፣ ከምዕራቡ ዓለም ወደ አፍሪካ የተጣሉ ሁሉንም ዐይነት የቴክኖሎጂ ውጤቶች ያካትታል። ኤልያስ ወደተለያዩ የገበያ ቦታዎች እየሔደ፣ እነዚኽን ቁሶች ሰብስቦ በመልክእ፣ በዐይነት እና በመሳሰሉት እየለየ፣ ይህን የመሰለ ረቂቅ ጥበብ ይፈጥራል። ከሥራዎቹ የሚበዙት፣ የከተማውን ሕይወት የሚያስቃኙ ሲኾኑ፣ ሐሳቦቹ ከመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ጋራ ይመሳሰላሉ። ለምሳሌ አንድ ሰው፥ የኾነ ካርታ ሊመስለው ይችላል።”

ኤልያስ፣ እነዚኽ የቴክኖሎጂ ውጤት የኾኑ ቁሶችን በብዛት የሚያገኛቸው፣ ዐዲስ አበባ ውስጥ በተለምዶ ምን ያለሽ ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው። ቁሶቹን የሚጠቀመው፣ በቴክኖሎጂ እድገት፥ በሰው ልጆች እና በአካባቢ ላይ እየደረሰ ያለውን ተጽእኖ አጉልቶ ለማሳየት ነው፡፡ የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን ጥንቃቄ ካልታከለበት፣ “በተወጠረ ገመድ ላይ የመጓዝ ያክል ነው፤” ሲል አደጋውን ያመላክታል።

ኤሊያስ፣ ለጥበብ ሥራው የሚጠቀምባቸውን የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች እስኪያገኝ ድረስ፣ ዓመታት ሊወስዱበት ይችላሉ፡፡ የወዳደቁ እቃዎች ኾነው እንዲታዩ ግን አይፈልግም። ይልቁንም ፍላጎቱ፣ ቁሶቹ ባስቆጠሩት ዘመን ልክ፣ የነበራቸው ታሪክ እና ጠቀሜታ ጎልቶ እንዲታይ ነው።

ሮይ ፓደከን እንደሚሉት ፣ ኤልያስ በረቂቅ የጥበብ ሥራዎቹ ከሚያነሣው ሐሳብ በተጨማሪ፣ በአፍሪካ ብቻ የሚገኙ የጥበብ ይዘቶችን መጠቀሙ፣ ሥራዎቹ ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ ረድቶታል።

“በሥራዎቹ የሚያነሣው ሐሳብ ብቻ ሳይኾን፣ የቀረቡበት ባህላዊ መንገድም ልዩ ያደርጋቸዋል። የኤልያስ ሥራ ብዙ ነገር አለው። ስለ አካባቢ ያነሣል። ብዙ ሰው የማያውቀውን፣ ከምዕራቡ ዓለም የሚወጡት የኤሌክትሪክ ተረፈ ምርቶች የት እንደሚወገዱም ያሳያል። በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ነው የሚጣሉት። ከዚያ በተጨማሪ ሥራው፣ ከጨርቃ ጨርቅ እና ሽመና ጋራ፣ በተለይ በአፍሪካ ከሚገኙ ባህላዊ የጥበብ ዐይነቶች ጋራ ምስላዊ ግንኙነቶችን ይፈጥራል።”

ኤልያስ፣ ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ትምርህት ቤት ከተመረቀ በኋላ ባሉት ዓመታት፣ “ታይ ሮፕ” ከተሰኘው ተከታታይ የጥበብ ሥራው ባሻገር፣ ከጭቃ፣ ከጨርቅ፣ ከፕላስቲክ እና ከዕንጨት፣ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን አውጥቷል። የእጅ አሻራን ተመስሎ በጭቃ ውስጥ ኾኖ የተሠራን ጎጆ ጨምሮ፣ የተወሰኑ

የሥራ ውጤቶቹ፣ ዐዲስ አበባ በሚገኘው እና ከባልደረባው ደራሲ እና አንትሮፖሎጂስት መስከረም አሰግድ ጋራ በከፈተው፣ “ዜማ ሙዚየም” ውስጥ ይገኛል፡፡ ሙዚየሙ፥ እንደ ዳማከሴ እና አሪቲ የመሳሰሉ ልዩ ልዩ ሀገር በቀል ዕፀዋትንና ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ድረስ የሕፃናት ትምህርት ቤት እንደሚገኙበት ይገልጻል።

የኤልያስ የጥበብ አሻራ፣ እ.አ.አ. በ2019 ዓ.ም.፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብዣ፣ በዐዲስ አበባ ታላቁ ቤተ መንግሥት ቅጽር በተሠራው “የአንድነት ፓርክ” ላይም አርፏል፡፡ በተጨማሪም፣ በቁጥር በማያስታውሳቸው፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የኦፔራ ትዕይንቶች ላይ በሠራቸው አልባሳት፣ መድረኮች እና ቅርፆች ላይ ቀርበው አድናቆትን አትርፈዋል።

/ሮይ ፓደከን ያነጋገረው ስካት ስተርንስ ነው፣ ኤልያስ ስሜን ያነጋገረው እስክንድር ፍሬ ነው። ስመኝሽ የቆየ ሁለቱን ቃለ ምልልሶች አጣምራ ዘገባውን አሰናድታለች። ሙሉውን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG