በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈጻሚ በጡረታ ተገለሉ


ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም
ፎቶ ፋይል፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስፈጻሚዎች ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገ/ማርያም ባለባቸው የጤንነት እክል ምክንያት ባላፉት ስድስት ወራት በዩናይትድ ስቴትስ ህክምናቸው እየተከታተሉ መሆኑን በመግለጽ ከጡረታ ጊዜያቸው አስቀድሞ ለመገለል ያቀረቡትን ጥያቄ የአየር መንገዱ ቦርድ መቀበሉን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመለከተ፡፡

መግለጫው ሥራ አስፈጻሚው ሙሉ ትኩረታቸውን በግል ጤንነታቸው ላይ ማድረግ ስለሚገባቸው ያለ ማቋረጥ የቅርብና ሙሉ ክትትል የሚሻውን የአየር መንገድ ሥራ መስራት ይሳናቸዋል ብሏል፡፡

አቶ ተወልደ አቅርበውታል የተባለውን ይህንኑ የሚገልጽ ጥያቄ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 14፣ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የተመለከተው መሆኑን የገለጸው ቦርዱ፣ አቶ ተወልደ ከጊዜያቸው አስቀድመው ጡረታ ለመውጣት ያቀረቡትን ጥያቄ የተቀበለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

አቶ ተወልደ፣ አየር መንገዱ ከአስርት ዓመታት በላይ በማገልገል ለአየር መንገዱ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም መግለጫው አመልክቷል፡፡

አየር መንገዱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ወደ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የተስፈነጠረ እድገት እንዲያመጣ ከ33 አውሮፕላኖች ወደ 130 አውሮፕላኖች እንዲያድግ ከ3 ሚሊዮን ወደ 12 ሚሊዮን መንገደኞች እንዲያደግ በማድረግ በኩል የበኩላቸውን ከፍተኛ የአመራር ብቃትና ስኬት ያሳያል ሲል መግለጫው አመልክቷል፡፡

ቦርዱና ከፍተኛ የማኔጅመነት አባላትና መላው የአየር መንገድ ሠራተኞች አቶ ተወልደ ከገጠማቸው የጤንነት እክል እንዲያገግሙ በመመኘት ለእርሳቸው ያላቸውን አክብሮት ይገልጻሉም ብሏል፡፡

ቦርዱ አዲሱን ሥራ አስፈጻሚ በቅርብ ይፋ እንደሚያደርግ በመግለጫው ያስታወቀ ሲሆን ከፍተኛ ብቃትና አገልግልት የነበራቸው ከአቶ ተወልደ በፊት የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥራ አስኪያጅ የነበሩትን አቶ ግርማ ዋቄን የአየር መንግዱ ሥራ አስኪያጅ በቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ በቅርቡ መሾሙንም መግለጫው አመልክቷል፡፡፡

XS
SM
MD
LG